የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲን በአፍሪካ ስመ-ጥር የፖሊስ ተቋም ለማድረግ እየተሰራ ነው

155

አዲስ አበባ፣ ጥር 07/2014(ኢዜአ)የኢትዮጵያ ፖሊስ ዩኒቨርሲቲን በአፍሪካ ስመ-ጥር የፖሊስ ተቋም ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ተናግረዋል።


ከ1939 ዓ.ም ጀምሮ በትምህርትና ስልጠና ዘርፍ በርካታ የፖሊስ አባላትን እያበቃ የሚገኘው ዩኒቨርሲቲው የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ እዮቤልዩ አክብሯል።
በእዮቤልዩ ስነስርዓቱ ላይም የላቀ የስራ አፈጻጸም ላስመዘገቡ የፓሊስ አባላት የማእረግ እድገት ተሰጥቷል።


ማእረግ በማልበስ መርሃ-ግብሩ ላይ የፌደራል ፖሊስ ወንጀል መከላከል ዘርፍ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ፣የፌደራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል ዘላለም መንግስቴ እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰላም እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ቀነዓ ያደታ ተገኝተዋል።


ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መላኩ ፋንታ ዩኒቨርሲቲውን በአፍሪካ ስመ-ጥር ከሆኑ የፖሊስ ተቋማት መካከል አንዱ ለማድረግ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ከዩኒቨርሲቲው በተጨማሪ በሀገሪቱ ያሉ የፖሊስ ተቋማት ህዝብን ይበልጥ እንዲያገለግሉ የማብቃት ስራ እንደሚከናወንም ገልጸዋል፡፡


ፖሊስ በእውቀት ላይ የተመሰረተ የህግ የበላይነትን የማስከበር ስራ እንዲያከናውን ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰው፤ ይህ ተግባር ተጠናክሮ እንዲቀጥል አስገንዝበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ምክትል ኮሚሽነር ጀነራል መስፍን አበበ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ለ43ኛ ጊዜ በዲፕሎማ እንዲሁም ለ21ኛ ጊዜ ደግሞ በሰርተፊኬት ሰልጣኞችን ማስመረቁን አስታውሰዋል፡፡


በፖሊሲንግ እና ህግ በዲግሪ እንዲሁም በ'ክሪሚኖሎጂ' በማስተርስ መርሃግብር ስልጣኞችን ማስመረቁንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡


በዛሬው እለት የማዕረግ እድገት ያገኙ የፖሊስ አባላት ዩኒቨርሲቲው በሚሰጠው አገልግሎት የላቀ አፈጻጸም ያስመዘገቡ አመራሮችና ሰራተኞች መሆናቸውንም ነው የተናገሩት፡፡


የማዕረግ እድገት ያገኙ የፖሊስ አባላትም የተሰጣቸው እውቅና የተሻለ ስራ ለመስራት የሞራል መነቃቃት እንደፈጠረላቸው ተናግረዋል፡፡


ብቁ የፖሊስ ኃይል ለመፍጠር ጠንክረው እንደሚሰሩም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም