የአክሲዮን ገበያ ተደራሽነትን በማስፋት የስራ ፈጣሪዎችን የፋይናንስ እጥረት መቅረፍ ይገባል

267

አዲስ አበባ፣ ጥር 07/2014(ኢዜአ) የአክሲዮን ገበያ ተደራሽነትን በማስፋት ስራ ፈጣሪዎች የሚያጋጥማቸውን የፋይናንስ እጥረት መቅረፍ እንደሚገባ የፋይናንስ ባለሙያዎች ገለጹ፡፡


የአክሲዮን ገበያ (ስቶክ ማርኬት) ለሀገር ኢኮኖሚ ስላለው አበርክቶ የፋይናንስ ተቋማት አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች የተገኙበት ውይይት በአዲስ አበባ ተካሂዷል፡፡


የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማህበራት ፕሬዚዳንት መሰንበት ሸንቁጤ በዚህ ወቅት የስራ ፈጣሪዎች ዋነኛ ችግር የፋይናንስ እጥረት መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ለስራ መነሻ የሚሆን ገንዘብ በብድር ለማግኘት ከፍተኛ ውጣ ውረድ መኖሩን ገልጸው፤ የአክሲዮን ገበያ የፋይናንስ ችግርን በመቅረፍ ረገድ ከፍተኛ ሚና እንዳለው አብራርተዋል፡፡


ስራ ፈጣሪዎች በእጃቸው ያለውን አቅም ለአክሲዮን ሽያጭ በማቅረብ የፋይናንስ ችግራቸውን መቅረፍ እንደሚችሉም ነው ያብራሩት፡፡


የአክሲዮን ገበያ የስራ እድልን ለማስፋትና የንግድ ስርዓትን ለማዘመን ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ቢሆንም በኢትዮጵያ በሚፈለገው ደረጃ ጥቅም ላይ ሳይውል መቆየቱን አስታውሰዋል፡፡


መንግስት አሁን ላይ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን መቅረፍ የሚያስችል ተቋማዊ አደረጃጀት መፍጠሩን ገልጸው፤ አዲስ የተቋቋመውን “የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን” በዚህ ረገድ ለአብነት አንስተዋል፡፡


መንግስት የግል ሴክተሩን የሚያበረታታ ፖሊሲና የህግ ማዕቀፍ ማውጣቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡


የፖሊሲ ማሻሻያው የቁጠባ ባህልን በማዳበር ህጋዊ የጥሬ ገንዘብ ዝውውር እንዲኖር እንደሚያደርግም ተናግረዋል፡፡


የፋይናንስ ባለሙያ የሆኑት አቶ አስራኤል ካሳ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የአክሲዮን ገበያ በሚፈለገው ደረጃ ተግባራዊ ባለመሆኑ በሀገር ኢኮኖሚ እድገት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ መፍጠሩን ገልጸዋል፡፡


የአክሲዮን ገበያ ዜጎች ያላቸውን አነስተኛ ሃብት በማሰባሰብ ኢንቨስት የሚያደርጉብትን እድል እንደሚፈጥር ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ መንግስት ዘርፉን የሚመለከቱ ማሻሻያዎችን ማድረጉ ለሀገር እድገት ፋይዳው ጉልህ መሆኑን አብራርተዋል፡፡


ዜጎች በጥቂት ገንዘብ አክሲዮን በመግዛት የታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ባለቤት እንዲሆኑ እድል እንደሚፈጥር የተናገሩት የግል ኦዲተሮች ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ ዮዲት ካሳ ናቸው፡፡


በመሆኑም ዘርፉ ይበልጥ እንዲጎለብት ባለድርሻ አካላት የሚጠበቅባቸውን ሚና ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት፡፡