ከሶስቱ ሀገራት የተውጣጡ ምሁራን የህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅን የተመለከተ ሳይንሳዊ ጥናት ያደርጋሉ

55
አዲስ አበባ ግንቦት 9/2010 ከኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን የተውጣጡ ምሁራን የታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ውሃ አሞላልና አለቃቀቅን በተመለከተ ሳይንሳዊ ጥናት እንደሚያካሂዱ የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር አስታወቀ። የሶስቱ አገሮች መሪዎች በሰጡት መመሪያ መሰረት ከሀገራቱ የተውጣጡ የውሃ ጉዳዮች ሚኒስትሮች፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችና ደህንነቶች በብሄራዊ ቴክኒካል ኮሚቴ እየታገዙ በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያደረጉት ውይይት ከሶስት ቀን በፊት መጠናቀቁ ይታወሳል። ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳብራሩት አገሮቹ በመጨረሻ የደረሱበት ስምምነት ያለገለልተኛ አካል ጣልቃ ገብነት በራሳቸው መፍትሄ እንዲፈልጉ መሰረት የጣለ ነው። የአማካሪው ድርጅት ጥናት ረጅም ጊዜ ሊወስድ ስለሚችል የግድቡ ውሃ አሞላል፣ የውሃ አለቃቀቅ እንዲሁም የሚያሳድረው ተፅዕኖ በአገሮቹ ባለሙያዎች እንዲጠና ኢትዮጵያ ቀደም ብላ ሀሳብ ማቅረቧን ጠቅሰው 'በመጨረሻም ስምምነት ላይ ተደርሷል' ብለዋል። ከሶስቱ አገሮች የተውጣጡ አምስት አምስት ምሁራን በጋራ ጥናት ካከናወኑ በኋላ በመጨረሻ ሁሉንም የሚያስማማ ሀሳብ እንደሚመጣ ገልጸዋል። የባለሙያዎቹ ጥምረት በግድቡ ላይ ሶስተኛ ወገን ጣልቃ እንዳይገባ እንደሚያደርግ ገልጸው በሶስት ወር ውስጥ ጥናቱ ተጠናቆ ለአገሮቹ የውሃ ሚኒስትሮች ለውይይት ይቀርባል ብለዋል። ከዚህ በተጨማሪ አገሮቹን የሚያስተሳስሩ መሰረተ ልማቶችን ለመስራትና በመሪዎች ደረጃ በየስድስት ወሩ ተራ በተራ በየአገሮቹ ዋና ከተሞች ውይይት ለማድረግ ከስምምነት ላይ መደረሱን ገልፀዋል። በዚህም ቅድሚያ ሊሰሩ የሚገባቸው መሰረተ ልማቶችና ፈንዱን ለማቋቋም የሚያግዙ ሰነዶች ላይ ሰኔ 26 እና 27 ቀን 2010 ዓ ም በካይሮ ውይይት ይደረጋል ብለዋል። ከዚህ በፊት አማካሪው ድርጅት አገሮቹ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጥ እንዳልነበር አስታውሰው አሁን  አማካሪ ያቀረበው የመነሻ ሀሳብ፣ የወደፊት አካሄዱና አገሮቹ ለሚያነሷቸው ጥያቄዎችም ምላሽ እንዲሰጥ ስምምነት ላይ መደረሱን ተናግረዋል። አማካሪው በሚያቀርበው ሪፖርት ላይ ሶስቱም አገሮች የሚሰጡት አስተያየትና የሚያቀርቡት ጥያቄ አማካሪው መልስ እንዲሰጥበት በጋራ ደብዳቤ በማዘጋጀት ለአማካሪው እንዲቀርብ ስምምነት መደረጉን ጠቁመዋል። ስምምነቱ የሶስቱንም ጥቅም ያስከበረ መሆኑን ጠቅሰው የግድቡ ግንባታ አሁንም ያለመስተጓጎል እንደቀጠለ ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም