አመልድ የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የሚደረገውን ስራ እያገዘ ነው

126

ባህር ዳር፤ ጥር 7 ቀን 2014 (ኢዜአ) አመልድ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የሚከናወኑ ስራዎችን እያገዘ መሆኑን የድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር አስታወቁ።

የአመልድ 12ኛ ጠቅላላ ጉባኤ በባህር ዳር ከተማ መካሄድ ጀምሯል። አቶ አገኘሁ በጉባኤው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት፤ አመልድ ላለፉት ዓመታት የክልሉን ህዝብ ኑሮ ለማሻሻል የተለያዩ የልማት ስራዎችን ሲያከናውን ቆይቷል።

በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎችን በመደገፍና የስራ እድል በመፍጠር የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን አውስተዋል።

የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመስኖ እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በመገንባት የላቀ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ተናግረዋል።

ድርጅቱ በአሸባሪው ህወሓት የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት የሚደረገው ሁሉን አቀፍ እንስቃሴ እያገዘ መሆኑን ገልጸዋል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ይልቃል ከፋለ በበኩላቸው፤ አመልድ በክልሉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማቶችን እያከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።

አርሶ አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርጉ አነስተኛ የመስኖ አውታሮችን በመገንባት፣ የስራ እድል በመፍጠር፣ በመጠጥ ውሃና በደን ልማት ሃብት በመሳተፍ ጉልህ አስተዋጽኦ እያበረከተ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ በማቋቋም የበኩሉን እየተወጣ መሆኑን ነው ርዕሰ መስተዳድሩ ያመለከቱት።

በጉባኤው የድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ አባላትና ጥሪ የተደረገላቸው አካላት እየተሳተፉ ሲሆን የድርጅቱ አዳዲስ የስራ አመራር ቦርድ እንደሚመረጡ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም