በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መዋዕለ ነዋያችንን በማውጣት ሀገራችንን ለመገንባት ዝግጁ ነን

57

ጥር 6/2014/ኢዜአ/ በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ መዋዕለ ነዋያቸውን በማውጣት ሀገራቸውን ለመገንባት መዘጋጀታቸውን ዳያስፖራዎች ገለጹ።


የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከዳያስፖራ ኤጀንሲ ጋር በመተባበር በአምራች ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት ካላቸው ዳያስፖራዎች ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ተወያይቷል፡፡

በምክክር መድረኩ የተገኙት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር መላኩ አለበል በአምራች ዘርፉ ያሉትን ሰፊ እድሎች በመጠቀም ሀገሪቱ ተጠቃሚ እንድትሆን በጋራ መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

መንግስት ዘርፉን ለማሳደግ ልዩ ትኩረት በመስጠት በቀጣዮቹ 10 ዓመታት ከዘርፉ 10 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘትና ለአምስት ሚሊዮን ዜጎች የስራ እድል ለመፍጠር እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

ዳያስፖራዎች በአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ሰፊ እድሎች ላይ መዋዕለ ነዋያቸውን በማውጣት ከዘርፉ እንዲጠቀሙና ኢትዮጵያ ከሌሎች ሀገራት ጋር ልትወዳደር የምትችልበትን ሁኔታ መፍጠር እንደሚገባ ጠቁመዋል።

ነዋሪነቱ በሲልቨር ስፕሪንግ ሜሪላንድ የሆነው ኢንጂነር ሚካኤል ያደታ ከኖረባቸው ሀገራት በርካታ ተሞክሮዎችን ይዞ መምጣቱን ገልጾ፥ በአምራች ዘርፉ ለመሰማራት ፍላጎትአለኝ ብሏል።

በመንግስት አሰራር በኩል የሚስተዋሉ ክፍተቶች ቀስ በቀስ የመፍታት ስራዎች እንዲከናወኑም ጠይቋል።

ኑሮውን በኖርዌይ ያደረገው አላሚን ፋሪስ በበኩሉ በቆዳው ዘርፍ በርካታ እድሎች መኖራቸውን መገንዘቡን በመጥቀስ፥ ራሱንም ሀገሩንም ለመጥቀም እንደሚሰራ ተናግሯል።

ለመስራት እድሎች የተመቻቹ መሆናቸውን ያነሳው የሲያትል ነዋሪው ያሬድ ተካሲማ ባሉት የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሰማራት ዝግጁ መሆኑን ጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም