አሸባሪው ህወሃት በለኮሰው ጦርነት ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ህጻናትን በቋሚነት እንደግፋለን

77

ባህር ዳር፣ ጥር 05 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት ለኩሶት በነበረው ጦርነት ወላጆቻቸውን ያጡና ችግር ላይ የወደቁ ህፃናትን በቋሚነት እንደሚደግፉ የዳያስፖራ አባላት አስታወቁ።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የመንግስትን ጥሪ ተቀብለው ወደ ሀገር ቤት ከገቡ ዳያስፖራዎቸ ጋር በችግር ላይ የሚገኙ ህፃናት በቋሚነት በሚደገፉበት ሁኔታ ላይ ትናንት ተወያይቷል።

ከውይይቱ ተሳታፊዎች መካከል በኖርዌይ የኢትዮጵያ ማህበር ሊቀመንበር አቶ ልዑል አለማየሁ እንደገለጹት፤ ከአሁን ቀደም  በአማራና በአፋር ክልሎች  በአሸባሪ ህወሓት ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች 3 ሚሊዮን ብር በማሰባሰብ ድጋፍ አድርገዋል።

አሸባሪው ቡድን ንጹሃን ላይ በፈጸመው ግፍ ጉዳት ያጋጠማቸውን ለመደገፍ በኖርዌይ ከሚኖሩ የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ጋር መወያየታቸውን አስታውሰዋል።

በዚህም ወላጆቻቸውን ላጡ ህፃናት አስፈላጊውን ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል።

አቶ ያለው ታረቀኝ የተባሉ ዳያስፖራ በአሸባሪው ህወሓት ምክንያት ወላጆቻቸውን ላጡና በባህር ዳር ህፃናት ድጋፍና እንክብካቤ ማዕከል ለሚገኙ ህፃናት በየዓመቱ 20 ሺህ ብር ድጋፍ ለማድረግ ቃል መግባታቸውን ገልጸዋል።

''በርካታ ቁጥር ያላቸው ህፃናት ወላጆቻቸውን በማጣታቸው ያላሳዳጊ መቅረታቸው ያሳዝናል'' ያሉት ከኖርዌይ የመጡት ወይዘሮ ሰዋሰው ስለሺ፤ "ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናትን አንድ ዲያስፖራ ለአንድ ቤተሰብ በሚል መርህ በቋሚነት በምንችለው ሁሉ ለማገዝ ዝግጁ ነን" ብለዋል።

የአማራ ክልል ሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ አስናቁ ደረስ እንደገለጹት አሸባሪው ህወሓት በወራራ በቆየባቸው የክልሉ ሰባት  ዞኖች በዜጎች ላይ የከፋ ሰብአዊ ጉዳትና  ቁሳዊ ውድመት አድርሷል።

በርካታ ቁጥር ያላቸው ህጻናትም ወላጆቻቸውን በሞት  ማጣታቸውንና ከወላጆቻቸው ጋር ለመለያየት መገደዳቸውን አስረድተዋል።

ህጻናት በጦርነቱ ምክንያት ለከፋ ችግር የተጋለጡና አስቸኳይ ሁለንተናዊ ድጋፍ የሚሹ መሆናቸውን አመልክተዋል።

''በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ህፃናትን መርዳትና ተንከባክቦ ማሳደግ የሁላችንም ሃላፊነት ሊሆን ይግባል'' ያሉት ወይዘሮ አስናቁ  በተለይ የዳያስፖራ አባላት አስፈላጊውን  ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም