"በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ አባላት በአገራቸው ጉዳይ በአንድ ልብ ቆመዋል"

101

አዲስ አበባ ፣ ጥር 05/2014(ኢዜአ) በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት የኢትዮጵያ ጉዳይ አንድ አድርጓቸው አገራቸውን ለመደገፍ በጋራ ቆመዋል ሲሉ በአውስትራሊያ ሜልቦርን ነዋሪ የሆኑት አቶ ተክሌ ላምቦሮ ገለጹ።

ኮሚዩኒቲው መንግስት ያቀረበውን የመልሶ ግንባታ ጥሪ በመቀበል እንቅስቃሴ መጀመሩንም ተናግረዋል።

በአውስትራሊያ ሜልቦርን ነዋሪ የሆኑት አቶ ተክሌ ላምቦሮ በዚያ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን አገሪቷን ለመደገፍ ከመቼውም ጊዜ በላይ መነሳሳታቸውን ለኢዜአ ገልጸዋል።

"በኢትዮጵያ ያለው ወቅታዊ ሁኔታ ዳያስፖራውን በአገሩ ጉዳይ  አንድ እንዲሆን አድርጎታል፤ ልቡና ቀልቡ ኢትዮጵያ ላይ ብቻ ሆኗል" ነው ያሉት።

በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት የኢትዮጵያዊነትና የአገር ፍቅር ስሜታቸው ልብን የሚያሞቅና አስደሳች እንደሆነም ተናግረዋል።

በዚያ ያለው ማኅበረሰብ ለተፈናቀሉ ወገኖች፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከልና ለወቅታዊ አገራዊ ጥሪዎችና የልማት ፕሮጀክቶች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝም ነው የገለጹት።

ለአውስትራሊያ መንግስት በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማብራሪያ በመስጠትና ደብዳቤም በመጻፍ ዲፕሎማሲያዊ ጥረት እየተደረገ እንደሆነም አቶ ተክሌ ተናግረዋል።

የአውስትራሊያ መንግስት ባለስልጣናትም 'በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በቅርበት እየተከታተልን ነው' የሚል ምላሽ እንደሚሰጡም ጠቅሰዋል።

የአገሪቷ መገናኛ ብዙሃን ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ሚዛናዊና ትክክለኛ እይታ እንዲኖራቸው በየጊዜው እውነታውን የማሳወቅ ስራ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በቅርቡም በተለያዩ የአውስትራሊያ ከተሞች የ'በቃ' /#NoMore/ ዘመቻ አካል የሆኑ ሠላማዊ ሠልፎች መካሄዳቸውን አቶ ተክሌ አስታውሰዋል።

በሠልፎቹ ላይ ዳያስፖራው አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ የሚያደርጉትን ጫና በመቃወም ድምጻቸውን ማሰማታቸውንና ለኢትዮጵያ ያላቸውን አጋርነት ማሳየታቸውን ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ መንግስት በመልሶ ግንባታው ሂደት ዳያስፖራው ድጋፍ እንዲያደርግ ያቀረበውን ጥሪ ተከትሎ በአውስትራሊያ የኢትዮጵያ ኮሚዩኒቲ አባላት እንቅስቃሴ መጀመሩን ገልጸዋል።

ኮሚዩኒቲው በገንዘቡ፣ በእውቀቱና በሙያው ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ እየተላለፈ ይገኛል ያሉት አቶ ተክሌ ዳያስፖራው ለእናት አገሩ የሚጠበቅበትን ግዴታ መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።

መንግስት በአውስትራሊያ የሚገኘው ዳያስፖራ አገሩን በቋሚነት እንዲደግፍ ከኮሚዩኒቲው ጋር ያለውን ትስስር የሚያጠናክርበት አሰራር ሊያበጅ ይገባልም ብለዋል።

ዳያስፖራውም እንዲሁ ኢትዮጵያን የመለወጥ አቅም ስላለው ያልተቋረጠ ድጋፍ ማድረግ እንደሚገባው አመልክተዋል።

በአውስትራሊያ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያን በተቋቋመው 'ሴቭ ኢትዮጵያ' የተሰኘ ጥምረት አስተባባሪነት በሕዳር 2014 ዓ.ም በተዘጋጀ የበይነ መረብ መድረክ ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ 178 ሺህ የአውስትራሊያ ዶላር መሰብሰቡ የሚታወስ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም