የፋይናንስ ተቋማት ለፊልም ስራዎች የብድር አቅርቦት እንዲያመቻቹ ተጠየቀ

82

አዲስ አበባ ፣ጥር 05/2014(ኢዜአ) የፋይናንስ ተቋማት ለፊልም ስራዎች የብድር አቅርቦት እንዲያመቻቹ ተጠየቀ።

ወደ ዲጂታል ፊልም የተቀየረው ኂሩት አባቷ ማነው ፊልም ዛሬ ተመርቋል።

በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ሒሩት አባቷ ማነው ፊልም ከ57 ዓመታት በኋላ ወደ ዲጂታል ፊልም ተቀይሮ ተመርቋል።

የኂሩት አባቷ ማነው ፊልም በልማት ባንክ ብድር የተሰራ ሲሆን የፊልሙ ባለቤት ብድሩን መመለስ ባለመቻሉ ለረጅም ዘመናት በባንኩ ተወርሶ ቆይቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ኂሩት አባቷ ማነው?' ለጥበብ ሰዎች ዐይን የገለጠ እና የፊልም ስራ አዲስ ምዕራፍን የከፈተ ነው ብለዋል።

ከንቲባዋ ፊልሙ ለሕዝብ ዕይታ እንዲቀርብ ላደረጉ አካላት በሙሉ ምስጋናቸውን ቸረዋል።

በበርካታ አገራት የፊልም ጥበብ ዘምኖ ማንነታቸውን ለማሳየትና ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስከበር እየተጠቀሙበት መሆኑን ገልፀዋል።

የብዝሀ ታሪክ ባለቤቷ ኢትዮጵያ ግን የፊልም ስራን ቀድማ ብትጀምርም በተለያዩ ምክንያት ይህን ዕድል አልተጠቀመችበትም ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን መንግስት ትልቅ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ከንቲባዋ አንስተዋል::

ሁሉም ዜጋ ጥበብን በበጎ መልኩ እንዲጠቀምባት፣ ትውልድን እንዲቀርጽበት፣ አብሮነት እንዲያጎለብትበት፣ ማንነታችንና ባህላችንን ጨምሮ እሴቶቹን እንዲያንፀባርቅበት መስራት ይገባል ብለዋል።

የአዲስ አበባ ባህል ኪነ ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሒሩት ካሳው፤ ልማት ባንክ በብድር የወረሰውን ፊልም ለ40 ዓመታት በጥንቃቄ አስቀምጦ በማስረከቡ ያላቸውን አድናቆት ገልፀዋል።

ባንኩ ከ57 ዓመታት በፊት ለፊልም ጥበብ ስራ የሰጠውን ብድር አድንቀው፣ ይህ በፋይናንስ ተቋማት ለኪነ ጥበብ ስራ የሚሰጠው የብድር አሰጣጥ ታሪክ አሁንም እንዲጀመር ጠይቀዋል።

በምድረ ቀደምቷ ኢትዮጵያ የፊልም ጥበብ ቀደም ብሎ ቢጀምርም እንደ ዕድሜው ባለመራመዱ አገር ልታገኘው የምትችለውን ጥቅም አሳጥቷል ብለዋል።

አሁን የፊልም ፖሊሲው በዘርፉ ጥበብ ዕድገት አስተዋፅኦ በሚያደርግ ሁኔታ ወደ ስራ ገብቷል ነው ያሉት።

በተግዳሮቶችም ውስጥ ሆኖ የፊልም ጥበብ ዕድገት መነቃቃት እያሳየ በመሆኑ፣ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ለዘርፉ እድገት የበኩሉን ሚና እንዲወጣ በጋራ እንዲሰሩ አደራ ብለዋል።

ለሒሩት አባቷ ማነው ፊልም ተዘጋጅቶ ድጋሚ እንዲቀርብ ያደረጉ ግለሰቦችና ተቋማት ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

በኢትዮጵያ 57 ዓመታትን ያስቆጠረው የመጀመሪያው ፊልም (ስነ- ራዕይ) 'ኂሩት አባቷ ማነው' ፊልም ተደራሽነቱን ለማስፋት በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ፈቃድ በ2012 በአቶ ፋሲል አብርሐ አማካኝነት ወደ ዲጂታል ተለውጧል።

ፊልሙ 1 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ርዝመት ያለው ሲሆን፤ ባለ 45 ሚሊ ሜትር ሆኖ በከፍተኛ ጥራት ባለው ቪዲዮ ቅጅ በአዲስ አበባ ሲኒማ ቤቶች አስተዳደር ድርጅት ተዘጋጅቷል።

በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎችና የኪነ ጥበብ ቤተሰቦች በታደሙበት የምረቃ ስነ ስርዓቱ ተካሂዷል።

ፊልሙ ጥር 7 ቀን 2014 ዓ.ም በብሔራዊ ቴአትር፣ በሲኒማ አምባሳደር በሲኒማ አምፒርና በሲኒማ ኢትዮጵያ ይመረቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም