በክፍለ ከተማው ለተደራጁ 107 ኢንተርፕራይዞች የመስሪያና የመሸጫ ቦታ ተሰጠ

59

ጥር 04 ቀን 2014(ኢዜአ) የቂርቆስ ክፍለ ከተማ በተለያዩ የሙያ መስኮች ለመሰማራት ለተደራጁ 107 ኢንተርፕራይዞች የመስሪያ እና የመሸጫ ቦታ ሰጠ።

ቦታዎቹ የተላለፉት ለአካል ጉዳተኞች፣ ከስደት ተመላሾች እና አዲስ ለተደራጁ ወጣቶች መሆኑ ተመልክቷል።

የመሸጫ ቦታዎቹ ደግሞ ከዚህ ቀደም በህገ ወጥ መንገድ ተይዘው የነበሩ እና በተለያዩ ምክንያቶች ጥቅም ላይ ሳይውሉ ተዘግተው የነበሩ ናቸው።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሙባረክ ከማል፤ በዛሬው እለት ለ225 ዜጎች  የስራ እድል ተጠቃሚ የሚያደርጉ 107 ኢንተርፕራይዞች የመስሪያ እና የመሸጫ ቦታ ቁልፍ አስረክበናል ብለዋል።

ለመስሪያ ቦታ ቁልፍ የተረከቡ ወጣቶችም ባገኙት አድል መደሰታቸውን ተናግረዋል።

ወጣት ሚሚ ለገሰ ቲኪ "በዚህ የስራ ፈጠራ ላይ በአጠቃላይ 26 ልጆች አለን የምንሳተፍ 19 ኞቻችን መስማት የተሳነን ነን እና ይሄ ቦታ ማስፋፊያ ስለተሰጠን በጣም ደስ ብሎናል፤ ተጨማሪ የስራ እድልን ለመፍጠር እያሰብን ነው እስከ 200 ለሚሆኑ ሰዎች የስራ እድሎችን የመፍጠር አቅም አለን ለወደፊትም ደግሞ የተሻለ ነገር እንሰራለን ብለን ተስፋ እንደርጋለን" ብላለች።

ሌላኛዋ የመስሪያ ቦታ ቁልፍ የተረከበችው ወጣት ሀሰና ጁሀር በጨርቃ ጨርቅ የተለያዩ የአልባሳት ስፌት ስራ ለመሰማራት መዘጋጀቷን ገልፃለች።

ወጣት ኡመር ሀዲ ባገኘው እድል መደሰቱን ገልፆ በፍጥነት ወደ ስራ ለመግባት መዘጋጀቱን ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም