በሲዳማ ክልል የ51 መንገዶች ግንባታና ጥገና ተጠናቆ ለአገልግሎት በቅተዋል

55

ሀዋሳ፤ ጥር 04/2014 (ኢዜአ)፡ በሲዳማ ክልል ከ558 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ አዲስ ከሚገነቡና ከሚጠገኑ መንገዶች መካከል የ51ዱ ስራቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃታቸውን የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ትናንትና ዛሬ በሎካ አባያ፣ በቦርቻ፣ ደራራ፣ ብላቴና ሀዋሳ ዙሪያን ጨምሮ ከ10 በላይ ወረዳዎች እየተሰሩ ያሉ የመንገድ መሰረተ ልማቶችን ጎብኝተዋል።

በጉብኝቱ ወቅት የክልሉ መንገድ ልማትና ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ላታሞ እንደገለጹት ሲዳማ በክልል ከተደራጀ በኋላ የክልሉ መንግስት የህዝቡን የመሠረተ ልማት ጥያቄዎች ትርጉም ባለው መልኩ ለመመለስ እየሰራ ነው።

ባለፈው አመት ለመንገድ ልማት 326 ሚሊዮን ብር በመመደብ ስራ ላይ ማዋሉን ጠቁመው በ2014 በጀት ዓመት ከ558 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ 632 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው 83 አዲስ የገጠር መንገድ ፕሮጀክት፣ 20 ዘመናዊ ድልድዮችና 1 ሺህ 400 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ 139 የጥገና ፕሮጀክቶች ግንባታ መጀመሩን አመልክተዋል።

እስካሁን በተካሄደው ስራ የ51 መንገዶች አዲስ ግንባታና ጥገና ተጠናቆ ለአገልግሎት መብቃታቸውን አስታውቀዋል።

ከተጠናቀቁት መካከል 274 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያላቸው አዲስ መንገዶችና 358 ኪሎ ሜትር ጥገና የተደረገላቸው መንገዶች ለትራፊክ ክፍት ተደርገው አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በዚህ ዓመት ግንባታቸው ከተጀመሩት 20 ዘመናዊ ድልድዮች ውስጥም ስድስቱ ተጠናቀው ለአገልግሎት መብቃታቸውን አመልክተዋል።

የተጠናቀቁ መንገዶችን ጨምሮ ግንባታቸው በሂደት ላይ የሚገኙ ሁሉም ፕሮጀክቶች በበጀት ዓመቱ መጨረሻ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቁ ከ30 በላይ የወረዳ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ እንደሚያደርጉ አመልክተዋል።

የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አራርሶ ገረመው በበኩላቸው ያልተጠናቀቁ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜና ጥራት ተጠናቀው ለአገልግሎት እንዲውሉ አስፈላጊው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

የመንገዶቹ ስራ በክልሉ ያሉ የልማት ኮሪደሮችን በሚያስተሳስር መልኩ እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት የቢሮ ሃላፊው የተጠናቀቁት የመንገድ ፕሮጀክቶች ለዚህ ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መንገዶቹ የግብርና ምርቶችን ወደ ይርጋለም የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ በሚፈለገው ጊዜና መጠን ለማጓጓዝ ምቹ ሁኔታ መፍጠራቸውን አመልክተዋል። የመንገዶቹ መገንባት የአካባቢውን ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ በማነቃቃት አርሶ አደሩንና ኢንዱስትሪዎችን ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።

የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ማህበራዊ አገልግሎቶችን በቅርበት ማግኘት ለማይችሉ የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎችን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ያለሙ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በክልሉ ከቴክኒክና ሙያ እንዲሁም ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የምህንድስና ሙያ ምሩቃንን በተማሩበት መስክ ወደ ሥራ ለማስገባት በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልፀው በዚህ ረገድ በርካታ ወጣቶች ኮንትራት ወስደው በመንገድ ሥራ ፕሮጀክቶች ተሳታፊና ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የጭነት መኪና አሸከርካሪ መልካሙ ጴጥሮስ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት ከአባያ ዙሪያ ወረዳ እስከ ሎካ አባያ ወረዳ ባሉ አራት ወረዳዎች የግብርና ምርት እንደሚያመላለስ ገልፅዋል። ከዚህ በፊት ወረዳዎቹን የሚያገናኝ ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ባለመኖሩ ተሸከርካሪዎች ለተደጋጋሚ ጉዳት ይጋለጡ እንደነበር አስታውሷል።

ጭነቶችን በሚፈለገው ፍጥነት ለማድረስ አስቸጋሪ እንደነበር ጠቁሞ አሁን ላይ ችግሩ በመቃለሉ ምስጋና አቅርቧል። የሎካ አባያ ወረዳ ነዋሪ ወይዘሮ ሀና ለማ በበኩላቸው በአካባቢያቸው ምንም አይነት የመንገድ መሰረተ ልማት ባለመኖሩ ወላዶችንና ህሙማንን ወደ ጤና ተቋም ለመውሰድ ችግር መሆኑን ተናግረዋል።

በችግሩ ምክንያት ሰዎች በህክምና እጦት ህይወታቸውን እንደሚያጡ ጠቁመዋል። አሁን ላይ ችግሩን ለመፍታት የሚያስችል የመንገድ መሰረተ ልማት ሥራ በአካባቢያቸው በመጀመሩ እሳቸውን ጨምሮ የአካባቢው ህብረተሰብ ደስተኛ መሆኑን አስረድተዋል።

የመንገዱ ስራ ሲጠናቀቅ ያመረቱትን የሰብል ምርት በቀላሉ ወደ ገበያ ለመውሰድም ሆነ ከገበያ የሚፈልጉትን ለመግዛት እንደማይቸገሩ አመልክተዋል።

ለመንገድ ልማቱ ከተያዘው በጀት ውስጥ 516 ሚሊዮን ብር የሚሆነው በክልሉ መንግስት የሚሸፈን ሲሆን ቀሪው ከመንገድ ፈንድ በተገኘ ድጋፍ የሚሰራ መሆኑ ተመላክቷል።

በጉብኝት መርሃ ግብሩ ላይ የሲዳማ ክልል የመንገድ ልማትና ትራንስፖርት ፣ የፋይናንስ ፣ የፕላንና ልማት ቢሮዎች እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጨምሮ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም