የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በአፋር ክልል በአሸባሪው ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በአፋር ክልል በአሸባሪው ቡድን ለተፈናቀሉ ወገኖች 3 ሚሊዮን ብር ድጋፍ አደረገች
ሰመራ፤ ጥር 4/2014(ኢዜአ) የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በአፋር ክልል በአሸባሪው ቡድን ወረራ ለተፈናቀሉ ወገኖች ዛሬ 3 ሚሊዮን ብር ለግሳለች።
ድጋፉን የተረከቡት የአፋር ክልል ተጎጂ ወገኖች የሃብት አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪ አቶ መሐመድ አህመድ እንዳሉት፤ የሽብር ቡድኑ ሴቶች፣ ህጻናትና አቅመ-ደካሞችን እንዲሁም የኃይማኖት ተቋማትን የጥቃት ኢላማ በማድረግ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል።
ተጎጂዎቹን መልሶ ለመቋቋም ብሎም ወቅታዊ ሀገራዊ የህልውና ፈተናዎችን በድል ለመሻገር የኃይማኖት መሪዎችና ተቋማት ቁልፍ ሚና እንዳላቸው ነው የገለጹት።
በገንዘብ፣ ቁሳቁስና በሥነ-ልቦና በመደገፍና በማጽናናት ወገናዊና መንፈሳዊ ሃላፊነታቸውን በመወጣት ላይ እንደሚገኙም ተናግረዋል።
ከዚህ አኳያ የኢትዮጵያ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች ያደረገችው ድጋፍ ሁነኛ ማሳያ መሆኑን በመጥቀስ ምስጋና አቅርበዋል።
ኢትዮጵያውያን በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች ሲያደርጉ የቆዩትን ድጋፍ እንዲቀጥሉም አስተባባሪው ጠይቀዋል።
የቤተክርስቲያኗ ዋና ፀሐፊ ቢሾፕ ጌታሁን ሌምቤቦ በበኩላቸው፤ ቤተክርስቲያኗ በክልሉ ለሚገኙ የጦርነቱ ሰለባ ለሆኑ ወገኖች ድጋፍ ያደረገችው ሀገራዊና መንፈሳዊ ሃላፊነቷን ለመወጣት እንደሆነ ተናግረዋል።
ቤተክርስቲያኗ በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች የምታደርገውን ሰብዓዊ ድጋፍ እንደምትቀጥልም ተናግረዋል።