መንግሥት የተወሰኑ እስረኞችን መፍታቱ ለዘላቂ ሰላም መስፈን ፋይዳው የጎላ ነው

55

ሶዶ፣ ጥር 04 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግሥት የተወሰኑ እስረኞችን ክስ አቋርጦ መፍታቱ ለሀገሪቱ ዘላቂ ሰላም መስፈን ከፍተኛ ሚና እንዳለው የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ምሁራን አስታወቁ።

በዩኒቨርሲቲው የሕግ መምህር የሆኑት አብነት ጨመረ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የኢትዮጵያን ዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልጽግና ማረጋገጥ የሁሉንም ዜጎች ተሳትፎ ይጠይቃል።

በመሆኑም መንግስት ሁሉን አካታች ምክክር ለማድረግ የወጠነውን ሀሳብ ተግባራዊ ለማድረግ  የተወሰኑ ግለሰቦችን ክስ አቋርጦ ከእስር መፍታቱ አስፈላጊ መሆኑን አስምረውበታል።

በአገራዊ በምክክሩ የሚፈለገው ውይይት ተደርጎ ውጤት እንዲመጣ ዋጋ ተከፍሎ አካታች እንዲሆን መደረጉ በምክክሩ ገንቢ ሚና እንደሚኖረው አስረድተዋል።

"ውሳኔው ለሀገር ዘላቂ ሠላም መስፈን ካለው ፋይዳ አንፃር ሲመዘን ጠቀሜታው ይጎላል በመሆኑ የሚደገፍ ነው" ብለዋል።

ወደፊት ሊካሄድ በታሰበው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ላይ ከእስር የተፈቱ ግለሰቦች ሀሳባቸውን ለማንጸባረቅ ጭምር እድል ስለሚኖራቸው የተሻለ ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችል ጠቁመዋል።

በሀገር አቀፍ ደረጃ የሚካሄደው ምክክር ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ትልቅ ድርሻ እንዳለው ጠቁመው፤በተለይ ሰላም እንዲሰፍን ሁሉም ዜጋ በሀገሩ ጉዳይ ላይ በንቃት መሳተፍ እንዳለበት ተናግረዋል።

በዩኒቨርሲቲው ሌላኛው የህግ መምህር ነብዩ ማርቆስ በበኩላቸው ባለፉት ጊዜያት በሀገር ላይ የደረሰው  ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ዲፕሎማሲያዊ ችግሮች ቀላል የማይባል መሆኑን ጠቅሰዋል።

ችግሮችን ለማስቆም አስፈላጊውን ዋጋ በመክፈል የሀገሪቱን ሰላም ለማረጋገጥ በሚያስችሉ ቀጣይ ስራዎች ላይ ትኩረት ሊሰጥ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ዘለቄታዊ ሰላምን ለማስፈን የመፍትሔ ሀሳቦች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ጠቁመው፤ በሀገሪቱ ላይ የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊና ዲፕሎማሲያዊ ጫና ለመቋቋም ለሀገሪቱ ጥቅም ትኩረት መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

በምክክሩ ላይ የሚሳተፍ ማንኛውም ግለሰብ ይዞ የሚቀርበው ሃሳብ የሀገር ጥቅምን የሚያስጠብቅና ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ አዎንታዊ ሚና ያለው ሊሆን እንደሚገባም አመላክተዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም