መንግስት በአጎራባች አካባቢ ለሚታየው የፀጥታ ችግር ዘላቂ መፍትሄ ሊሰጥ ይገባል - የአማሮ ወረዳ ነዋሪዎች

52
ሀዋሳ ነሀሴ 22/2010 መንግስት በአጎራባች አካባቢ ለሚታየው የፀጥታ ችግር ዘላቂ መፍትሄ በመስጠት የልማት ተሳታፊና ተጠቃሚነታቸውን እንዲያረጋግጥላቸው በሰገን አካባቢ ህዝቦች ዞን የአማሮ ወረዳ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ነዋሪዎቹ በዶክተር አብይ አህመድ አመራር በሀገሪቱ እየመጣ ያለውን የሰላም፣ የልማት፣ የመደመርና የአንድነት ለውጥ እንደሚደግፉ ዛሬ በኬሌ ከተማ ባደረጉት ሰላማዊ ሰልፍ አስታውቀዋል፡፡ ኢዜአ ያነጋገራቸው የወረዳው ነዋሪዎች እንዳሉት ዶክተር አብይ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ቦታውን ከተረከቡ ጊዜ አንስቶ እየተመዘገበ ያለው ለውጥ ተስፋቸውን አለምልሟል፡፡ የኬሌ ከተማ ነዋሪ አቶ ደምሴ አየለ እንዳሉት የወረዳው ነዋሪዎች ለውጡን በሙሉ ልብ የሚደግፉት ቢሆንም የራሳቸውን ድርሻ እንዳያበረክቱ በአጎራባች አካባቢ የሚደርስባቸው ጥቃትና የፀጥታ ችግር እንቅፋት ሆኖባቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ከአማሮ ወደ ዲላ ሀዋሳ የሚወስደው መንገድ በመዘጋቱ ምክንያት ያለው እንቅስቃሴ መገደቡንና ህዝቡ ለእንግልት መዳረጉን  ገልጸዋል፡፡ ሌላው የከተማው ነዋሪ ወጣት አለሙሳ ለገሰ በበኩሉ  ''ወጣቱ በተለያዩ መስኮች ተደራጅቶ የስራ እድል ተጠቃሚ እንዳይሆን ባለው የጸጥታ ችግር ምክንያት ከፍተኛ ጫና እየደረሰበት ነው'' ብሏል፡፡ የመኪና መንገዱ ከመዘጋቱ ባለፈ በአካባቢው ባለው የጸጥታ ችግር በርካታ ወጣቶች ላይ ጉዳት መድረሱን ተናግሯል፡፡ የሰላማዊ ሰልፉ አስተባባሪ አቶ ሻሮን ሻርጮ እንዳሉት የወረዳው ነዋሪ በተለያዩ ጊዜያት ከአጎራባች አካባቢዎች ከሚደርስበት ጥቃት በተጨማሪ በመሰረተ ልማት ችግር ተጎጂ ሆኖ መቆየቱን ገልጸዋል፡፡ ዛሬ የተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ዋና አላማውም ይህን ችግር ለመንግስት ለማሳወቅና ነው ብለዋል፡፡ ወረዳው ከልማት አንጻር ከኬሌ - ደርባመነንና አርባምንጭ፤ ከጂጆላ - መዳይነ - አይኩረወ - ኢታቴ የተጀመረው መንገድ ሳይጠናቀቅ ለረጅም ጊዜ መቆየቱ አርሶ አደሩ ያመረተውን ምርት ለገበያ ለማቅረብና ነፍሰጡር እናቶችን ወደ ህክምና ስፍራ ለማድረስ እንደተቸገሩ አስታውቀዋል፡፡ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ አማኑኤል አብደላ በበኩላቸው ህዝቡ ያነሳውን የልማት ጥያቄ ለመመለስ የወረዳው አስተዳደር እንደሚሰራና አመራሩ ከህዝቡ ጎን እንደሚቆም ገልጸዋል፡፡ ዛሬ በአማሮ ኬሌ ከተማ በተካሄደው የድጋፍ ሰላማዊ ሰልፍ ላይ በወረዳው ከሚገኙ 35 ቀበሌዎች የተውጣጡ ነዋሪዎች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም