ዳያስፖራው አሸባሪው ህወሓትን የሚደግፉ ሃይሎችን በዓለም አደባባይ አጋልጧቸዋል- ዶክተር ድረስ ሣህሉ

57

ባህር ዳር ጥር4/2014(ኢዜአ) ''ዳያስፖራው ማህበረሰብ አሸባሪ ቡድኑን የሚደግፉ ሃይሎችን በዓለም አደባባይ እንዲጋለጡ አድርጓል" ሲሉ የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ድረስ ሣህሉ አስታወቁ።

የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ለዳያስፖራ አባላት የወንድማማችነትና የቤተሰብ የእራት ግብዣ ትላንት አካሄዷል።

ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው በዚሁ ወቅት እንደገለጹት ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ባንዳዎችና ጽንፈኛ ሃይሎች እንዲሁም በአንዳንድ ምዕራባዊያን ተጽዕኖ ስትፈተን ዳያስፖራው በግንባር ተሰልፎ ከሚዋደቀው ሃይል ያልተናነሰ ሥራ አከናውኗል።

"በዚህም ዳያስፖራው ማህበረሰብ አሸባሪውን ቡድን የሚደግፉ ሃይሎችን በዓለም አደባባይ በእርቃናቸው እንዲቀሩና እንዲጋለጡ አድርጓል" ብለዋል።

ዳያስፖራው በዲፕሎማሲው መስክ ያስመዘገበው ውጤት ዛሬ ለተገኘው ድል አስተዋጽኦ ማበርከቱንና የራሱንም ሀገራዊ ሃላፊነት መወጣቱን ዶክተር ድረስ ተናግረዋል።

የእራት ግብዣው የዳያስፖራው ማህበረሰብ ኢትዮጵያ ባስመዘገበችው ድል ላደረገው አስተዋጽኦ ክብር ለመስጠትና ለማመስገን እንደተዘጋጀም አስታውቀዋል።

አስተዳደሩ የዳያስፖራ ማህበረሰብ ለሚፈልገው ማንኛውም አገልግሎት ክፍት መሆኑን ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው አረጋግጠዋል።

"በምንኖርባቸው ሀገሮች ውስጥ ኢትዮጵያን ቀይ ዞን ውስጥ በማስገባት ወደ ሀገር ቤት እንዳንመጣ ሲሰራ ነበር" ያሉት ደግሞ ከእንግሊዝ የመጡት አቶ ጋሻነህ አምቢሳ ናቸው።

ዳያስፖራው ወደ ሀገሩ መጥቶ ወገኖቹን እንዲጎበኝና ሀገሩን ተዘዋውሮ እንዲመለከት ላበቁና ለሀገራቸው ዳር ድንበር መከበር ለተዋደቁ ጀግኖች ምስጋና አቅርበዋል።

''ጊዜው መከባበር፣ መተሳሰብ፣ መተማመንና መግባባት የሚፈለግበት ነው'' ያለው ደግሞ በእራት ግብዣ ስነ ስርዓቱ ላይ የታደመው አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) ነው።

"ስለ አንድ ሀገር ነው የምናወራው" ያለው አርቲስት ስለሺ፣ የተለያዩ ሀሳቦች ቢመጡም እነዚህን ሃሳቦች በጋራ በማየት "ከችግር የምንወጣበት ጊዜ ላይ እንገኛለን" ብሏል።

በስነ ስርዓቱ የከተማው አመራሮች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወካዮችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎች ታድመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም