ዳያስፖራዎች በኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሳተፍ ተዘጋጅተዋል

67

ጥረ 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ባሉ የተለያዩ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን ዳያስፖራዎች ተናገሩ።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት የመጡ ዳያስፖራዎች የተሳተፉበት የኢንቨስትመንት ፎረም በአዲስ አበባ ተካሂዷል።

በፎረሙ ላይ በኢትዮጵያ ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮች፣ ማበረታቻዎችና የአሰራር ማሻሻያዎች ላይ በተለያዩ የመንግስት የስራ ሃላፊዎች ገለጻ ተደርጎላቸዋል።

በጤና፣ በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ፣ በቱሪዝም፣ በገቢና ወጪ ንግድ፣ በማምረቻው፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮችና ሌሎችም ዘርፎች ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችና እድሎች ማብራሪያ ተሰጥቷቸዋል።

በመሆኑም ከተዘረዘሩት የኢንቨስትመንት አማራጮች በፈለጉት ዘርፍ በመሰማራት የአገራቸውን ምጣኔ ሃብት ለማነቃቃት የበኩላቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀርቦላቸዋል።

በወጪና ገቢ ንግድ ላይ ያለውን አለመመጣጠን ለማስተካከልም በዘርፉ እንዲሰማሩ የተጠቆመ ሲሆን ቀልጣፋ የፈቃድ አሰጣጥ ስርአት መዘርጋቱ ተገልጿል።

ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት ለትርፍ ብቻ ሳይሆን አገርና ህዝብን ሊጠቅሙ በሚችሉ ዘርፎች ላይ እንዲሰማሩ ተጠይቀዋል።

የዳያስፖራ አባላት ወደ መጡበት አገር ሲመለሱም በአገራቸው ያሉ የኢንቨስትመንት አማራጮችንና እድሎችን  በማስተዋወቅ አምባሳደር እንዲሆኑም እንዲሁ።

በፎረሙ የተሳተፉ የዳያስፖራ አባላትም የቀረቡ የኢንቨስትመንት አማራጮችን በማጤን በተለያዩ ምቹ የኢንቨስትመንት አማራጮች ለመሳተፍ ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የዳያስፖራ አባላት ኢንቨስት ለማድረግ ወደ ተግባር በሚገቡበት ወቅት የሚያጋጥሙ ችግሮችን በመጥቀስ አገር ያለችበትን ሁኔታ ከግምት በማስገባት መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።

ቀደም ሲል በኢንቨስትመንት የተሰማሩ የዳያስፖራ አባላት እያጋጠማቸው ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር መንግስት እንዲፈታ ጠይቀው ስራቸውን አጠናክረው ለመቀጠል ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል። 

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፤ በጨርቃጨርቅ፣ ቆዳ፣ ኬሚካልና ሌሎች በማምረቻው ዘርፍ በርካታ የስራ እድል ሊፈጥሩ የሚችሉ አማራጮችን ለዳያስፖራው አብራርተዋል።

በዳያስፖራው የተጠቀሱ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን መፍታት እንደ አንድ የህልውና ዘመቻ መወሰድ እንዳለበት ገልጸው ችግሮችን ተቋቁመው ኢንቨስት በማድረግ አገራቸውን እንዲያለሙ ጠይቀዋል።

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ነሜ ኢትዮጵያ በችግር ውስጥ ሆናም ባለፉት 5 ወራት ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር በላይ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት መሳቧን ገልፀው የዳያስፖራውን ድርሻ አስገንዝበዋል።

በዳያስፖራ ኢንቨስትመንት ፎረም የገንዘብ ተቋማት፣ የሪልስቴት አልሚዎች፣ የክልል ኢንቨስትመንት ቢሮዎችን ያካተተ ኤግዚቢሽን የተከፈተ ሲሆን የፊታችን አርብ ድረስ ይቆያል ተብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም