በርካታ ተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን የመድህን ሽፋን አባል አለመሆናቸው የተጎጂዎች ካሳ ክፍያ ላይ ችግር ፈጥሯል

103

ጥር 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በርካታ ተሽከርካሪዎች የሶስተኛ ወገን የመድህን ሽፋን አባል ባለመሆናቸው በተጎጂዎች የካሳ ክፍያ ላይ ከፍተኛ ችግር ማስከተሉን የመድህን ፈንድ አገልግሎት ድርጅት አስታወቀ።

ድርጅቱ ባለፉት ስድስት ወራት በትራፊክ አደጋ ለደረሰ ሞትና የአካል ጉዳት 29 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ ፈጽሟል።

ባለፉት ስድስት ወራት በትራፊክ አደጋ በደረሰ የአካል ጉዳት፣ ሞትና የሃብት ውድመት እንዲሁም የተከፈለውን የካሳ ክፍያ በተመለከተ ድርጅቱ መግለጫ ሰጥቷል።

የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አቶ ጀማል አባሶ በወቅቱ እንደተናገሩት፤ በሶስተኛ ወገን የመድህን ሽፋን አባልነት የተመዘገቡ ተሽከርካሪዎች ቁጥር አነስተኛ መሆኑ በተጎጂዎች የካሳ ክፍያ ላይ ችግር ፈጥሯል።

በኢትዮጵያ ካሉት 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ተሽከርካሪዎች ውስጥ የ3ኛ ወገን ሽፋን አባል ሆነው የተመዘገቡት 774 ብቻ በመሆናቸው ድርጅቱ ለከፍተኛ ወጪ መዳረጉንም ተናግረዋል።

የትራፊክ አደጋ እየተባባሰ በመምጣቱ በስድስት ወራት ብቻ በ5 ሺህ 831 ተሽከርካሪዎች ላይ የግጭትና መሰል አደጋዎች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ በዚህም ለ13 ሺህ 796 ተጎጂዎች የአስቸኳይ ጊዜ የህክምና እርዳታ እንዲያገኙ በማድረግ  9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ብለዋል።

በድርጅቱ በኩል አሽከርካሪዎች የ3ኛ ወገን የመድህን ሽፋን አባል እንዲሆኑ ጥረት ቢደረግም የሚፈለገው ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ ገልጸዋል።

በቀጣይ ወራት ለ16 ሺህ 583 ተሽከርካሪዎች 257 ሚሊዮን ብር በላይ የካሳ ክፍያ ለመፈጸም በሂደት ላይ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

በሰዎች ላይ አደጋ አድርሰው የሚሰወሩ አንዳንድ አሽከርካሪዎች ስላሉ የጉዳት ካሳውን ድርጅቱ ብቻ ለመክፈል የሚገደድበት አጋጣሚ እየተበራከተ መምጣቱንም ገልጸዋል።

በመሆኑም የተሽከርካሪ አደጋን ለመቀነስና ጉዳት ለሚያጋጥማቸው ወገኖች አፋጣኝ ድጋፍ ለመስጠት አሽከርካሪዎች የ3ኛ ወገን ምዝገባ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም