በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የዳያስፖራው ድጋፍ ወጥነት ባለው አሰራር ሊመራ ይገባዋል

80

ጥር 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም የዳያስፖራው ድጋፍ በተበታተነ ሳይሆን ወጥነት ባለው አሰራር ሊመራ እንደሚገባ በዘርፉ ጥናት ያደረጉ አንድ ምሁር ገለጹ።

በፈረንሳይ አገር የሚኖሩት ፕሮፌሰር ብዙነሽ ታምሩ፤ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት አሸባሪው ህወሃት በከፈተው ጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ከጉብኝታቸው በኋላም የጉዳቱ ሰለባ የሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎችን መልሶ በማቋቋም ላይ ጥናት ለማድረግ እንደተነሳሱ ገልጸዋል።

ፕሮፌሰር ብዙነሽ ታምሩ በአገረ-ፈረንሳይ ፓሪስ በሚገኝ አንድ ዩኒቨርሲቲ የስነ-መልከዓ ምድር (ጆግራፈር) ባለሙያ ሲሆኑ የጥናታቸው ትኩረትም በህብረተሰብ እድገትና የጉዳት ተጋላጭነት ላይ ነው።

በዚሁ ዙሪያ ኢትዮጵያን ጨምሮ በተለያዩ አገራት በርካታ ጥናቶችን አካሂደዋል።

በተለይም ሄይቲ በምትባል አገር  በፈረንጆቹ 2010  በደረሰው ርእደ መሬት ከ200 ሺህ በላይ ሰዎችን ለሞት በዳረገው አደጋ በመልሶ መቋቋም ላይ ከሌሎች ባልደረቦቻቸው ጋር በበርካታ ጥናታዊ ሥራዎች ተሳትፈዋል።

በዚህ ጥናት ከ50 በላይ የአገሪቱ ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ አስተምረው ማስመረቅ መቻሉን ገልጸው፤ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበርም ኢትዮጵያ ውስጥ ጥናቶችን አካሂደዋል።

የእናት አገር ጥሪን ተከትለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት ፕሮፌሰር ብዙነሽ፤ በአማራና አፋር ክልሎች ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ተዘዋውረው ከተመለከቱ በኋላ ጉዳቱን በተመለከተ ለጥናት ተዘጋጅተዋል።

ፕሮፌሰር ብዙነሽ ጥናታቸውን ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለማከናወን ሂደት ላይ ይገኛሉ።

በጥናቱ ወደ አገር ቤት ከመጡ የተለያዩ ምሁራን ጋር በጋራ ለማከናወን እንደተዘጋጁም ተናግረዋል።

በመስክ ምልከታቸው በሁለቱ ክልሎች የተመለከቱት ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት የከፋ መሆኑን ጠቅሰው በተለይም ዳያስፖራው በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ ማድርግ አለበት ብለዋል።

በጦርነቱ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና ተጎዱ ዜጎችን መልሶ ለማቋቋም ዳያስፖራ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያደርግበት መረዳጃ ወይም ኢንዶውመንት ማቋቋም ያስፈልጋል ብለዋል።

ይህ አይነቱ አሰራር የግሉን ዘርፍ የሰብዓዊ እርዳታ ተሳትፎ የሚያሳድግ፣ ዳያስፖራው ያለጥርጣሬ በቋሚነት ገንዘብ እንዲልክ እና እምነት እንዲኖረው የሚያስችል ስልት እንደሆነ አብራርተዋል።

በሚኖሩበት ፈረንሳይ አገር እንኳን ማህበራዊ ዋስትና ሥርዓት የመንግሰት ሳይሆን የግሉ ዘርፍ የሚያንቀሳቅሰው መሆኑን ጠቁመዋል።

በኢትዮጵያም ችግር ሲያጋጥም ከመደነጋገር ገለልተኛ የመረዳጃ ተቋም ቢመሰረት ውጤታማ ይሆናል፤ የላቀ ፋይዳም ይኖረዋል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ቅራኔና ጥላቻን በማስወገድ መከባበርና አንድነቱ የተጠበቀ ማህበረሰብና ለመፍጠር በትምህርት ሥርዓቱ ላይ የፖለቲካና የፖሊሲ ለውጥ እንደሚያሻ ምክረ ሃሳባቸውን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም