ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነትና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማይናወጥ አቋሟ ትቀጥላለች

67

ጥር 03 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያ የአፍሪካ አንድነትና ትብብር ተጠናክሮ እንዲቀጥል በማድረግ በማይናወጥ አቋሟ የምትቀጥል መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ ተናገሩ።

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ ኤጀንሲ "ፓን አፍሪካኒዝምና የዳያስፖራው ሚና" በሚል መሪ ሃሳብ ከዳያስፖራው ማኅበረሰብ አባላት ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ምክክር አካሂዷል።

በመርሃ ግብሩ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ፤ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ጉዳይ ሊናወጥ የማይችል አቋም ነው ያላት ብለዋል።

በርካታ የአፍሪካ አገራትና አፍሪካዊያን ለኢትዮጵያ የሚያሳዩት አጋርነት ኢትዮጵያ የፓን አፍሪካኒዝም ራዕይ እውን እንዲሆን ላሳየችው ያልተቋረጠ ድጋፍ መሆኑን አንስተዋል።

የቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ኔልሰን ማንዴላ በኢትዮጵያ ወታደራዊ ሥልጠና የወሰዱበትን አጋጣሚ ያስታወሱት ሚኒስትር ዴኤታዋ ይህም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላትን ውግንና አመላካች ነው ብለዋል።

በአፍሪካዊያን መካከል ያለው አንድነት ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ገልጸው ለዚህም ኢትዮጵያ ለአፍሪካ ያላት የማይናወጥ አቋም ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።  

የፓን አፍሪካኒዝምን እንቅስቃሴ ውጤታማ ለማድረግ በአፍሪካ ያለው ድኅነት ፈተና መሆኑን ጠቅሰዋል።

አህጉሪቱ የምትፈልገው የፖለቲካ ነጻነት አፍሪካ በድህነት እየዳከረች እውን ልታደርገው እንደማትችል ጠቁመው በአፍሪካ ድኅነትን መቅረፍ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራበት ይገባል ነው ያሉት።

በቅርቡ የተጀመረው የአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጠና በአፍሪካ አገራት መካከል የንግድ ትስስር በመፍጠር የፓን አፍሪካኒዝም ህልም አውን እንዲሆን ትልቅ እገዛ ይኖረዋል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ የተሳተፉ የዳያስፖራ አባላት በበኩላቸው የፓን አፍሪካኒዝም አስተሳሰብ በአህጉሪቱ ይበልጥ እንዲሰፋና መሰረት እንዲኖረው የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።

በእንግሊዝ አገር የዲፌንድ ኢትዮጵያ ኢሮፕ አስተባባሪ አቶ ዘላለም ጌታሁን፤ መላውን የጥቁር ሕዝብ በማስተባበር ለአፍሪካዊያን መብት ለመቆም እንሰራለን ብለዋል።    

ከእንግሊዝ አገር የመጣው የዳያስፖራ አባል ደረጄ ደስታም በተለይም በ 'no more' የ "በቃ" እንቅስቃሴ የአፍሪካዊያንን አንድነት ይበልጥ አጠናክሯል ብለዋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ የአፍሪካ አገራት የዳያስፖራ አባላት አገራቸው እንዲሁም አህጉሪቱ በኢኮኖሚ ጠንካራ የምትሆንበትን ምቹ ሁኔታዎች በመፍጠር ላይ ሊያተኩሩ ይገባል ነው ያሉት።

አፍሪካዊያን በተለያዩ መስኮች ላይ ያሉትን አፍሪካዊ የሆኑ እውቀቶችንና ክህሎቶቹን ለአፍሪካ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሄ ማዋል ይገባቸዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም