የሕዝብን ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡና በሁሉም ዘርፎች ለውጥ የሚያመጡ ስራዎችን ማከናወን ያስፈልጋል- አቶ ኦርዲን በድሪ

70

ሐረር፣ ጥር 3/2014 (ኢዜአ) ከወትሮው በተለየ መልኩ ለሕዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡና በእያንዳንዱ የስራ ዘርፎች ላይ ለውጥ የሚያመጡ ስራዎችን ማከናወን እንደሚገባ የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ አስገነዘቡ።

የክልሉ ካቢኔ የ100 ቀን የዕቅድ ክንውን አፈጻጸም ግምገማ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ በተገኙበት በሐረር ከተማ እያካሄደ ነው።

ርዕሰ መስተዳድር ኦርዲን በድሪ በዚህ ወቅት እንደገለጹት በክልሉ አዲስ መንግሥት ምስረታን ተከትሎ ሁሉም የዘርፍ መስሪያ ቤቶች የ100 ቀን ዕቅድ አዘጋጅተው ወደ ስራ ገብተዋል።

የግምገማው ዋና ዓላማም ዕቅዱ ምን ያህል ስኬታማ ማድረግ እንደተቻለ ለመመልከት ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንዲሁም የዘርፍ መስሪያ ቤቱ የተቀመጡ ዕቅዶችን በመፈተሽ፣ ጠንካራና ደካማ ጎኖችን በመለየት ለቀጣይ ስራ ለመዘጋጀት እንደሚረዳ ተናግረዋል።

በተለይ የ100 ቀን ዕቅዱ ከወትሮው በተለየና የክልሉን ሕዝብ ጥያቄ ምላሽ የሚሰጡ እና በእያንዳንዱ የስራ ዘርፎች ላይ ለውጥ የሚያመጡ ስራዎችን ለማከናወን ያላሳለሰ ጥረት ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

የክልሉ በግብርና፣ ፋይናንስና ኢኮኖሚ፣ገቢዎች፣የኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንድስትሪ እን ትራንስፖርት እና መንገድ ልማት ቢሮ የስራ አፈጻጸማቸውን አቅርበዋል።

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሚስራ አብደላ ቢሮው በሰብል እና እንስሳት ምርትና ምርታማነት ከማሳደግ፣ በተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ፣በምግብ ዋስትና እና በሌሎች ዘርፎች የተከናወኑ የአንድ ወር የክንውን እቅድ አፈጻጸም አቅርበዋል።

በዚህም በተለይ የሰብል ምርታማነትን ለማሳደግ በክልሉ 1ሺ 430 ሄክታር መሬት በበጋ መስኖ እየለማ መሆኑን እና 28 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ደግሞ በክላስተር በበቆሎ ሰብል የማልማት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።

9ሺ 486 ሄክታር መሬት ላይ የነበሩ የደረሱ ሰብሎችን መሰብሰብ መቻሉንና በእንስሳት እና በዓሳ ሃብት ልማት እንዲሁም በሴፍትኔት የተከናወኑ ስራዎችን አቅርበዋል።

በክልሉ ገቢን ከማሳደግ አኳይ በ100 ቀናት 104 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር ለመሰብሰብ ካቀደው ውስጥ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ 35 ሚሊዮን ብር መሰብሰብ መቻሉን የገለጹት ደግሞ የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ካሊድ አብዲ ናቸው።

የክልሉ የኢንተርፕራይዝ ልማትና ኢንድስትሪ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ሰሚራ ዩስፍ በበኩላቸው በክልሉ የሚስተዋለውን የስራ አጥነት ችግር ደረጃ በደረጃ ለማቃለል እየተሰራ መሆኑን ገልጸው ባለፉት 60 ቀናት ለ945 ዜጎች የስራ ዕድል መፈጠሩንም አስረድተዋል።

ቀደም ሲል በኢንተርፕራይዞች የተሰጠ ብድርን ለማስመለስ በተደረገው ጥረት ደግሞ 3 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር ማስመለስ መቻሉን ተናግረዋል።

የመድረኩ ተሳታፊዎች ከካሽ ሪጅስተር ማሽን ጋር በተያያዘ በክልሉ የገቢ አሰባሰቡ ክፍተት መኖሩን፣ ህገ ወጥ የትራንስፖርት ታሪፍ በታክሲዎች ላይ እንደሚታይ ጠቁመዋል።

እንዲሁም ብድር ከማስመለስ፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ከማሻሻል፣ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው መርሃ ግብር ከማጠናቀቅ፣ ህግን ከማስከበር አንጻር የሚታዩ ክፍተቶች መኖራቸውም አንስተው በስራ ዕድል ፈጠራ ላይ ሁሉም የዘርፍ መስሪያ ቤቶች መረባረብ እንደሚገባቸው ተሳታፊዎቹ አስገንዝበዋል።

ካቢኔው በቀጣይም በሌሎች የሚቀርቡ የዕቅድ ክንውን አፈጻጸምን ተመልክቶ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም