የግሉን ዘርፍና ክልሎችን በስፋት የሚያሳትፍ አዲስ የኢነርጂ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ተዘጋጀ

64

አዳማ፤ ጥር 03/2014(ኢዜአ) የግሉን ዘርፍና ክልሎችን በስፋት የሚያሳትፍና ለታዳሽ ሃይል ትኩረት የሰጠ አዲስ የኢነርጂ ልማት ረቂቅ ፖሊሲ ማዘጋጀቱን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚንስቴሩ ረቂቅ ፖሊሲውን ለማዳበር ያዘጋጀው የምክክር መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ እንደገለጹት፤ መድረኩ አዲስ የተዘጋጀው የሃይል ልማትና እድገት ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ክልሎች ካላቸው ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በንቃት እንዲሳተፉና በግብዓት እንዲያዳብሩ ለማስቻል ነው።

ፖሊሲው ፀድቆ ወደ ትግበራ ሲገባም የማህበረሰቡን የኢነርጂ ልማትና ፍላጎት ለማሟላት የጋራ ግንዛቤ እንዲኖርና ለተፈፃሚነቱ ለመረባረብ የሚረዳ ነው ብለዋል።


ነባሩ ፖሊሲ ክልሎች በራሳቸው እንዲተጋገዙ፣ አንዱ የአንዱን ክፍተት የሚሞላበትና ተሞክሮዎችን የሚያሰፉበት አማራጮች እንዳልነበረው አውስተዋል ሚኒስትሩ።


በተለይም በዘርፉ ልማት ዙሪያ ክልሎችና የግሉ ሴክተር በስፋት እንዳይሳተፉ ያደረገ ከመሆኑም ባለፈ በታዳሽ ሃይል ልማትና አጠቃቀም ዙሪያ ያሉትን ማነቆዎችን ለመፍታት የማያስችል መሆኑንም አመልክተዋል።


በአዲሱ ረቂቅ ፖሊሲ በታዳሽ ሃይል፣ በባዮ ጋዝ፣ ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች፣ በሶላር ኢነርጂና ንፋስ ሃይል ልማትና እድገት ላይ በቀጣይነት የሚከናወኑ ስራዎች ትኩረት እንደሚሰጣቸው ጠቅሰዋል።


የሃይል አጠቃቀም ክፍተትን በማሻሻልና ብክነትን በማስወገድ የሃይል አቅርቦቱን በቀጣይ 10 ዓመታት ሙሉ በሙሉ ተደራሽ እናደርጋለን ያሉት ሚኒስትሩ፤ በጥናትና ምርምር በመደገፍም በቤተሰብ ደረጃ የሃይል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በዘላቂነት እንደሚሰራ አብራርተዋል።


በሀገራችን ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት ሀብት ቢኖርም በባዮ ጋዝ አጠቃቀም ሰፊ ችግር መኖሩን የገለጹት ደግሞ የሚኒስቴሩ የኢነርጂ ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ሱልጣን ወሊ ናቸው።


አዲሱ ረቂቅ ፖሊሲ በታዳሽ ሃይል ልማት በተለይም በባዮ ጋዝና ማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎች ልማትና ስርጭት ላይ ያለውን የአመለካከትና የአጠቃቀም ማነቆዎችን ለመፍታት የሚያስችል ነው ብለዋል።


የማገዶ ቆጣቢ ምድጃዎችን ዲዛይን በአዲስ መልክ በማስጠናት ጥራትና አዋጭነታቸውን በማስፈተሽ ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም አመላክተዋል።


አዲሱ ፖሊሲ በዋናነት በውሃ ላይ ብቻ የተመሰረተውን የሃይል ልማት አማራጮችን ለማስፋትና የግሉን ሴክተር በዘርፉ በስፋት ለማሳተፍ የጎላ ሚና እንዳለው ተገልጿል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው መድረክ ሁሉም ክልሎች፣ የከተማ አስተዳደሮችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም