በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ ወደ አገር ቤት የገቡ ዳያስፖራዎች ደማቸውን ለመከላከያ ሰራዊት ለገሱ

67

አዲስ አበባ፣  ጥር 03/2014(ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጥሪ ተቀብለው ወደ አገር ቤት የገቡ ዳያስፖራዎች ደማቸውን ለመከላከያ ሰራዊት ለገሱ።

የሲቪክ ማህበራት ባለስልጣን "ደሜን ለወገኔ" በሚል ሃሳብ ባዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ በመገኘት ነው ዳያስፖራዎቹ ደማቸውን ለሰራዊቱ የለገሱት።

ከደም ለጋሾቹ መካከል ከካናዳ የመጡት ወይዘሮ ብርሃን ፍቃዱ "ለጀግናው መከላከያ ሰራዊት ደሜን በመለገሴ ከፍተኛ ኩራትና ደስታ ተሰምቶኛል" ብለዋል።

ለኢትዮጵያ ህልውና በጀግንነት እየተዋደቀ ለሚገኘው ሰራዊት ደም በመስጠቴ እድለኛ ነኝ ሲሉም ተናግረዋል።

በተለይም የዳያስፖራ አባላት የተቸገሩ ወገኖችን ከማገዝ፣ የወደሙትን መልሶ ከማቋቋምና ከመገንባት በተጨማሪ ለሰራዊቱ አለኝታ ሆነን መገኘት አለብን ብለዋል።

ከአሜሪካ ወደ አገር ቤት የገቡት አቶ ያረጋል ጠበቃው፤ ለወገን ደም መስጠት ህይወት ከማትረፍ በተጨማሪ አለኝታነትን የሚያሳይ በመሆኑ ደማችንን ለግሰናል ብለዋል።

"የእኔ ደም መለገስ ሰራዊቱ ለአገሩ ከከፈለው መሰዋእትነት አንፃር አነስተኛ ነው" ሲሉም ተናግረዋል።

በመሆኑም ለጀግናው የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት፣ ለህዝቡና ለአገር ህልውና የሚችሉትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አቶ ያረጋል አረጋግጠዋል።

የሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ጂማ ዲልቦ "ከተለያዩ የአለም ሃገራት መጥታችሁ ለአገራችሁ አለኝታነታችሁን ለማሳየት ደማችሁን በመለገሳችሁ ልትመሰገኑ ይገባል" ብለዋል።

የአገርን ጥቅም ለማረጋገጥ ባለስልጣኑ በሚሰራቸው ስራዎች ሁሉ ዳያስፖራው ከጎናቸው እንዲቆም ጠይቀው የአገራቸውን ጥሪ ተቀብለው የቁርጥ ቀን ደራሾች በመሆናቸውም አድናቆታቸውን ገልጸዋል።

በደም ልገሳ መርሃ ግብሩ ላይ የተሳተፉ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊያኑ ለአገራቸው ሁሌም አለኝታ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም