ከጫና የፀዳ የልማት አጋርነትን የሚሻ ዘመን

76

እ.አ.አ 1991 የጥር ወር መጀመሪያ ላይ የወቅቱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቺያን ቺቼን በኢትዮጵያ፣ ኡጋንዳ፣ ኬንያ እና ታንዛኒያ ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ማድረጋቸው በቻይና-አፍሪካ ግንኙነት አዲስ ምዕራፍ ከፋች ነበር።

ከዛን ጊዜ  ጀምሮ የፈረንጆቹ አዲስ ዓመት ሲብት አፍሪካ በየዓመቱ የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቀዳሚ የባህር ማዶ ጉዞ መዳረሻ ሆናለች። ባለፈው ሣምንት የቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋን ዪ በሦስት የአፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝትም የዚህ ባህላዊና ዲፕሎማሲያዊ ትስስር ቅጥያ ነው። 

ዋን ዪ ኤርትራን በማስቀደም የዚህ ዓመት የአፍሪካ ጉብኝታቸውን በአስመራ ጀመረዋል።  የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የኤርትራ ጉብኝት በዓለም አቀፍ ደረጃ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል።

ሌላው ሚኒስትሩ ኤርትራ እና ኬንያን የጉብኝት መዳረሻቸው አድርገው መምረጣቸው ቻይና ለአፍሪካ ቀንድ የሰጠችው የተለየ ትኩረት የምዕራባውያን ቀልብ በመሳቡ ጭምር ነው። እንደሚታወቀው የቻይና ታላቁ ስትራቴጂ (China’s Grand Strategy) አገሪቷን ወደ ቀደመው የታላቅነት ማማ መመለስ ነው። የከፍታ ጉዞውን ለማሳካት ድንበር ዘለል ኢንቨስትመንት እና የፋይናንስ ተደራሽነትን የመገንባት ሥራ የተለየ ትኩረት ተሰጥቶታል።

ይኸው ስትራቴጂ በአፍሪካ፣ በባህረ ሰላጤው ሀገራት፣ በእስያ እና በአውሮፓ ያለውን የመሰረተ ልማት፣ የንግድ እና የልማት ትስስር ማጠናከርን ታሳቢ ያደረገ ሲሆን ቤልት እና ሮድ ኢኒሼቲቭ (Belt & Road Initiative-BRI) ደግሞ የስትራቴጂው ማሳኪያ እንዲሆን ቁልፍ ቦታን ይዟል።

በአፍሪካ ቀንድ እና በባብ ኤል መንደብ የባህር ወሽመጥ ወሳኝ ጂኦ-ፖለቲካዊ ስትራቴጂ ያላት ኤርትራ በሯን ለቤጂንግ ክፍት ማድረጓ የቻይና ታላቅ የመሆን ግዙፍ ስትራቴጂ መሳካት ጠቃሚ ተደርጎ ይወሰዳል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርን ጉብኝት የተለየ የሚያደርገውም ይህን ዓለም አቀፍ የመሠረተ ልማት ግዙፍ ፕሮጀክት ቤልት ኤንድ ሮድ ኢኒሼቲቭን ኤርትራ በተቀላቀለች ማግሥት መሆኑ ነው። የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጃኦ ሊጂያን ጉብኝቱን አስመልክተው በሰጡት አስተያየት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዋን ዪ ጉብኝት በቻይና-አፍሪካ የትብብር ፎረም (FOCAC) የሚኒስትሮች ጉባዔ ላይ የተደረሱ ስምምነቶችን ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንዲገቡ ለማስቻልና አዳዲስ እርምጃዎችን ለመውሰድ ያለመ ነው። 

እሳቸው ይህንን ቢሉም የጂኦ-ፖለቲካ ተንታኞች የሚገልጹት ቻይና በአገሮች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ አለመግባት የቆየ ፖሊሲዋን መነሻ በማድረግ ጥቅሟን ታሳቢ ያደረገ አቋም መያዟን ነው። ለዚህም በማሳያነት የሚያነሱት የቻይና መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ አገራት ጉዳይን በቅርበት የሚከታተል ልዩ ልዑክ ልትሾም መሆኗን በመጥቀስ ነው።

በኪዮቶ ጃፓን የዶሺሻ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ጥናት መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር ሰይፉዲን አደም የልዩ መልዕክተኛው መሾም ቻይና የአፍሪካ ቀንድን ጂኦ-ስትራቴጂያዊ ጠቀሜታ በውል መገንዘቧን የሚያሳይ ነው ይላሉ። ቻይና በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ያላት ሃያልነትና እምነት እያደገ መምጣቱን እንደሚጠቁምም ተናግረዋል።

በዊልያም ፓተርሰን ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር የሆኑት ፕሮፌሰር አሮን ተስፋዬ ለሳውዝ ቻይና ሞርኒንግ ስታር እንደገለጹት፤ የአፍሪካ ቀንድ ወቅቱን የዋጀ አዲስ የፖለቲካ ገጽታ ለቻይና ዕድሎችን ፈጥሯል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋን ዪ ጉብኝት ቻይና በቀጣናው በተለይም በቀይ ባህር አካባቢ ትልቅ ተዋናይ መሆኗን ያሳያል ሲሉ በዋቢነት ይጠቅሳሉ።

ቻይና በባህረ ሰላጤው ሀገራት ቁልፍ ተዋናዮች ከሆኑት ሃይሎች ጋር ያላትን 'የደቡብ-ደቡብ' ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ወታደራዊ ግንኙነቷን ለማጠናከር ከፍተኛ ፍላጎት እንዳላት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ያለፈው ሣምንት ጉብኝት አንዱ ማረጋገጫ ነው። የቻይና የሲልክ ሮድ (Maritime Silk Road) እና የቀይ ባህር ዳርቻ ደህንነትን ለማረጋገጥ መሻቷ ትልቁ ምክንያቷ ነው ብለዋል።

ቻይና ልዩ መልዕከተኛ የመሾሟ ተገቢነት ላይ በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የሰብዓዊና ማህበራዊ ሳይንስ ብሔራዊ ኢንስቲትዩት የድህረ ዶክትሬት ጥናት ባልደረባ የሆኑት ዩ-ሻን ዉ፤ የሚሾመው ልዩ መልዕክተኛ ቻይናን “የአፍሪካ ኅብረትን ጨምሮ ከአፍሪካ ባለ ብዙ ወገን የሠላምና የደህንነት ጥረቶችን በተሻለ ሁኔታ እንድትደግፍ  እና እንድታስተባብር የሚረዳ ነው” ሲሉ ይሞግታሉ። የልዩ መልዕክተኛው መሾም በቀጣናው ያሉ ውስብስብ ችግሮችን ቻይና ተገንዝባ ለመፍትሄ አጋር የምትሆንበትን ዕድል እንደሚፈጥር ይናገራሉ።

እንደ ኢትዮጵያ ላሉ የአፍሪካ አገራት አዲስ አቀራረብ ይዛ ብቅ ያለችው ቻይና ከጣልቃ ገብነት እና ከጫና የፀዳ የልማት አጋርነ መሆን ችላለች። ይህ ደግሞ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለአፍሪካውያን የተሻለ አማራጭ ብቻ ሳይሆን የሚታይ ልማትን ማስገኘት ችሏል።

ቻይና በመላው አፍሪካ ዘመናዊ መንገዶችን፣ የባቡር ሀዲዶችን፣ ወደቦችን፣ የኃይል ማመንጫዎችንና ሌሎች የህዝብ መገልገያ መሰረተ ልማቶችን በመገንባት አጋርነቷን በተግባር ማሳየት ችላለች።

ኤርትራን፣ ኬንያን እና ኮሞሮስን የጎበኙት የቻይና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋን ዪ በዴሞክራሲና በሰብዓዊ መብት ሰበብ በሌሎች አገራት የውስጥ ጉዳይ ላይ የሚደረገውን ጣልቃገብነት እና ጠቅላይነት ቻይና መቼም እንደማትቀበለው እወቁት ብለዋል።

ቻይና የአፍሪካ ዋነኛ የልማት አጋር ሆናለች። ሌሎችም ጊዜ ካለፈበትና በፖለቲካዊ ቅድመ ሁኔታ ከታጀበው የልማት ድጋፍ አስተሳሰብ ወጥተው ራሳቸውን ለልማት አጋርነት ሊያዘጋጁ ይገባል። አሁን ላይ ዘመኑም ዓለምም የሚሹት ከጫና የፀዳ የልማት አጋርነት ብቻ መሆኑንም መገንዘብ ተገቢነት አለው። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም