ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች በሄክታር ከ100 ኩንታል በላይ የስንዴና ገብስ ማምረት ቻሉ

331

ጎባ፤ ጥር 3/2014 (ኢዜአ) የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን ተግባራዊ በማድረግ በሄክታር ከ100 ኩንታል በላይ ስንዴና ቢራ ገብስ በአንድ የምርት ወቅት መሰብሰብ እንደቻሉ በባሌ ዞን አጋርፋ ወረዳ ኢዜአ ያነጋገራቸው ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች አስታወቁ።

በዞኑ በ2013/2014 የምርት ወቅት በተለያዩ የሰብል ዘር ከለማው ከ260 ሺህ ሄክታር መሬት ውስጥ 80 በመቶው መሰብሰቡም ተመልክቷል፡፡

አርሶ አደሮች እንዳሉት፤ በመስመር መዝራት፣ ኩታ ገጠም አሰራር ፣ ምርጥ ዘር እና የግብርና ባለሙያዎች የምክር አገልግሎትን በአግባቡ ተግባራዊ ማድረጋቸው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ችለዋል፡፡

ከአጋርፋ ወረዳ አሊ ቀበሌ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች መካከል አቶ አህመድ ጠይብ ኡመር፤ በምርት ዘመኑ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችና ፓኬጆችን በመጠቀም ካለሙት የስንዴና ገብስ ማሳ የተሻለ ምርት መሰብሰብ እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡

በተለይ ከግብርና ምርምር ያገኙትን የስንዴ ዝሪያ ከነሙሉ ፓኬጅ በማልማታቸው በሄክታር 102 ኩንታል የስንዴ ምርት ለመጀመሪያ ጊዜ ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ከስንዴ ምርት በተጨማሪ በተመሳሳይ ካለሙት አንድ ሄክታር የቢራ ገብስ ማሳ 103 ኩንታል ምርት በመሰብሰብ ከፍተኛ ውጤት ማስመዝገባቸውን አመልክተዋል፡፡

ቀደም ሲል በተለምዶው አሰራር ከሁለቱም የሰብል ዓይነቶች በሄክታር ከ60 እስከ 75 ኩንታል ምርት ያገኙ እንደነበር አርሶ አደሩ በንጽጽር በማመላከት አስረድተዋል።

ለዚህ ውጤት ያበቃቸው በመስመር የመዝራት፣ የኩታ ገጠም አሰራርንና ሌሎችንም የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀማቸው እንደሆነ ነው አርሶ አደሩ የገለጹት።

በወረዳው ከሌሎች ግንባር ቀደም አርሶ አደሩ ጋር በኩታ ገጠም አስተራረስ ዘዴ ተቀናጅተው በማልማት ቀደም ሲል በሄክታር ከ50 ኩንታል በላይ አምርተው እንደማያውቁና አሁን ላይ 75 ኩንታል ስንዴ ማምረታቸውን ያስታወቁት ደግሞ አቶ ጣፋ ኤጄሬ ናቸው፡፡

በመስመር መዝራትን ጨምሮ ሌሎች የተሻሻሉ አሰራሮችንና የባለሙያ የምክር አገልግሎት መጠቀማቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸው ተናግረዋል፡፡

ሌላው አርሶ አደር አየለ ከበደ በበኩላቸው፤ ከዚህ በፊት በተለምዶ የግብርና አሰራር በሄክታር ያገኙ የነበረው የስንዴ ምርት ከ20 ኩንታል እንደማይበልጥ ነው የገለጹት፡፡

“በተለያዩ ጊዜያት በተሰጠን ስልጠናና የባለሙያ ድጋፍ የአመራረት ዘዴያቸውን በመቀየርና ከአካባቢያችን ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ጋር በኩታ ገጠም አስተራረስ በመደራጀታችን የስንዴ ምርትን ወደ 65 ኩንታል ማሳደግ ችያለሁ " ብለዋል፡፡

የባሌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አልይ መሐመድ እንዳመለከቱት፤ በ2013/2014 የምርት ዘመን በተለያዩ የሰብል ዘር  ከለማው ከ260 ሺህ ሄክታር መሬት መካከል 80 በመቶ የሚሆነው ተሰብስቧል፡፡

የአርሶ አደሩ የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችና ፓኬጆችን የመጠቀም ዝንባሌ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ በመምጣቱ የሚገኘው ምርት እየጨመረ መጥቷል ብለዋል፡፡

በአጋርፋ ወረዳ በሄክታር ስንዴ 102 ኩንታል እና ገብስ ደግሞ  103 ኩንታል መሰብሰቡ በማሳያነት ጠቅሰዋል፡፡

በዚህም በምርት ዘመኑ በዘር ከተሸፈነው መሬት ውስጥ 60 በመቶ የሚሆነው መሬት በመስመር የመዝራት ቴክኖሎጂን ጨምሮ ሌሎች 

ሙሉ የግብርና ፓኬጆችን ተግባራዊ በማድረግ የለማ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ኃላፊው እንዳሉት፤ በዞኑ በዘመኑ የእርሻ ስራ ላይ ከ98 ሺህ የሚበልጡ  አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 300 ሺህ ኩንታል በላይ ማዳበሪያና ምርጥ ዘር ጥቅም ላይ ውሏል፡፡

የተሻሻሉ የግብርና አሰራሮችን በመጠቀም በአጋርፋ ወረዳ ግንባር ቀደም አርሶ አደሮች ዘንድ የተመዘገበውን ውጤት ወደ ሌሎች የዞኑ አካባቢዎች በማስፋት የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ የገለጹት ደግሞ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አብዱልሀኪም አልይ ናቸው።  

በዞኑ የተሻለ የዝናብ ስርጭት በነበረባቸው ወረዳዎች  የተሻለ ምርት የመገኘቱን ያህል በቆላማና ወይና ደጋ አካባቢዎች በተፈጠረው የዝናብ እጥረት ምክንያት ለመሰብሰብ ከታቀደው አጠቃላይ ምርት ውስጥ የ25 በመቶ የምርት ቅናሽ ሊያጋጥም እንደሚችል በባለሙያ በተደረገ የድህረ ምርት ትንበያ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡

በዝናብ እጥረት ምክንያት ሊቀንስ የምችለውን ምርት በበጋ ስንዴ በመስኖ ለማካካስ ከ19 ሺህ በሚበልጥ ሄክታር ላይ የመጀመሪያው ዙር ስራ እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በባሌ ዞን በምርት ዘመኑ በተለያየ የሰብል ዓይነት ከለማው መሬት 9 ሚሊዮን ኩንታል የሚጠጋ ምርት ለመሰብሰብ እንደታቀደ ነው የተመለከተው፡፡ 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም