በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት ተፈናቅለው ከነበሩ ዜጎች መካከል 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑትን ወደ ቀያቸው መመለስ ተችሏል

69

ጥር 2/2014/ኢዜአ/ በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ምክንያት ተፈናቅለው ከነበሩ ዜጎች መካከል 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑትን ወደ ቀያቸው መመለስ መቻሉን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽን ገለፀ፡፡

በሽብር ቡድኑ ወረራ በአማራና አፋር ክልሎች ከቀያቸው ተፈናቅለው የነበሩ ዜጎችንና የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለማቋቋም ዳያስፖራው ድጋፍ እንዲያደርግም ጥሪ ቀርቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ኤጀንሲ ታስፋ /ቲች ኤንድ ሰርቭ አፍሪካ / ከተሰኘ ድርጅት ጋር በመሆን ያዘጋጀውና በድህረ ግጭትና መልሶ ግንባታ ላይ ያተኮረ ውይይት  በአዲስ አበባ ተካሄዷል፡፡

በውይይቱ የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣የጤና ሚኒስተሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ፣ የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ እና የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችና ዳያስፖራዎች ተሳትፈዋል፡፡

የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በዚሁ ወቅት አሸባሪው ህወሓት ምክንያት በአማራ ክልል 1 ነጥብ 4 ሚሊዮን እንዲሁም በአፋር ክልል 427 ሺህ ዜጎች  ከመኖሪያ ቀያቸው መፈናቀላቸውን ገልጸዋል።

በአማራ ክልል ከቀያቸው ከተፈናቀሉ ዜጎች መካከል 1 ነጥብ 2 ሚሊዮን የሚሆኑትን ወደ ቀያቸው መመለስ ተችሏል ነው ያሉት፡፡

በተመሳሳይ በአፋር ክልልም ዜጎችን ወደ ቀያቸው የመመለሱ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉን አንስተዋል፡፡

አሸባሪው የህወሃት ቡድን በፈጸመው ዝርፊያና ውድመት በርካታ ዜጎች ያለምንም ንብረት በባዶ እጃቸው እንደሚገኙ ጠቅሰው፤ በዚህም አርሶና አርብቶ አደሮች ለከፍተኛ ጉዳት መጋለጣቸውን ተናግረዋል፡፡

የሽብር ቡድኑ ታጣቂዎች የገበሬውን በሬና ዶሮ ሳይቀር አርደው መብላታቸውንም ነው ያነሱት፡፡

በመሆኑም በተለይ አርሶና አርብቶ አደሮች ወደ ምርት እስኪገቡ ድረስ ድጋፍ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የትምህርት ሚኒስትሩ ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ በበኩላቸው በኢትዮጵያ የትምህርት ስርዓት ውስጥ ስር ሰዶ የቆየ የጥራት ችግር መኖሩን አስታውሰዋል፡፡

ይህን ችግር  ለመቅረፍ ግብረ-ገብነትን የተላበሰና በሳይንስና ቴክኖሎጂ የበለጸገ ትውልድ ለማፍራት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ስርዓት ከሚታዩ ችግሮች መካከል አንዱ የቋንቋ ክህሎት ውስንነት መሆኑን አስታውስው፤ዳያስፖራው ከታች ጀምሮ እስከ በዩኒቨርስቲዎች አገራቸውን መጥተው እንዲያገግሉ ጥሪ አቅርበዋል።

በተመሳሳይ የጤና ሚኒስተሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የሽብር ቡድኑ በጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ውድመት ማድረሱን ተናግረው፤ ተቋማቱን መልሶ በመገንባት ረገድ ዳያስፖራው የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትሯ ዶክተር ኤርጎጌ ተስፋዬ አሸባሪ ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች በፈጸመው ጥቃት ህጻናት፣ሴቶችና አረጋዊያን ላይ ከፍተኛ አካላዊና ስነ-ልቦናዊ ጉዳት ማድረሱን አስታውሰዋል፡፡

የመልሶ ማቋቋም ስራውም ይህን ታሳቢ በማድረግ ሊከናወን እንደሚገባም ነው የጠቀሱት፡፡

አሸባሪ ቡድኑ የአውሮፕላን ማረፊያ ጣቢያዎችን ጨምሮ በከፍተኛ ወጪ በተገነቡ መንገዶች ላይ ጉዳት ማድረሱን የተናገሩት ደግሞ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትሯ ዳግማዊት ሞገስ ናቸው፡፡

በመሆኑም የወደሙ የትራንስፖርት መሰረተ ልማቶችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት ላይ ዲያስፖራው በእውቀቱና  በገንዘቡ ጭምር ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በውይይቱ የተሳተፉ ዳያስፖራዎች በበኩላቸው በመልሶ መቋቋም ስራዎች ላይ የሚጠበቅባቸውን ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም