በኢትዮጵያ የሚወጡ የደረጃ መስፈርቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ተቀናጅቶ መስራት ላይ ክፍተቶች አሉ-የደረጃዎች ኤጀንሲ

105
አዲስ አበባ ነሃሴ 22/2010 በቁሳቁሶችና አገልግሎቶች ላይ የሚወጡ የደረጃ መስፈርቶችን ተግባራዊ ለማድረግ ተቀናጅቶ መስራት ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን የኢትዮጵያ የደረጃዎች ኤጀንሲ አስታወቀ። የኤጀንሲው የደረጃ ዝግጅት ዳይሬክተር አቶ ይልማ መንግስቱ ለኢዜአ እንደገለጹት በዓለም አቀፍ ደረጃ አስገዳጅ ደረጃዎች የሚዘጋጁባቸው ጥቅም ላይ በሚውሉ ቁሳቁሶችና አገልግሎቶች ላይ ያሉ ችግሮችን ለማቃለል ነው። ደረጃዎች አስገዳጅና አስገዳጅ ያልሆኑተብለው በሁለት መልኩ የሚወጡ ሲሆን ይሕም ከአካባቢ፣ ከሕብረተሰብ ጤንነትና ያልተፈለገ የንግድ ውድድርን ለመከላከል የሚቀመጡ ናቸው። በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ 201 አስገዳጅና ከ11 ሺህ በላይ አስገዳጅ ያልሆኑ ደረጃዎች እንዳሉ አስረድተዋል። እነዚህን የሚዘጋጁ ደረጃዎች ተግባራዊ ለማድረግና ሕብረተሰቡ የሚያገኝው አገልግሎት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ለማስቻል የተቆጣጣሪ አካላት ተሳትፎ በሚፈለገው መልኩ እየሰሩ አለመሆኑን ነው የሚገልጹት። "ደረጃዎች መዘጋጀታቸው ብቻ በቂ አይደለም" ያሉት አቶ ይልማ በየደረጃው የሚገኙ አካላት በተለይ የሚፀድቁ አስገዳጅ ደረጃዎች ስራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ እንደሚገባቸው ነው ያስረዱት። ተቆጣጣሪ አካላት ከኤጀንሲው ደረጃዎችን እየወሰዱ ማስተግበር የሚገባቸው ቢሆንምይሕ ሲሆን አይታይም ፤ለዚህም ዋነኛው ምክንያቱ በቅንጅት ለመስራት እየተሔደበት ያለው ርቀት አናሳ መሆኑ ነው ብለዋል። በዓለምና በአገር አቀፍ ደረጃ የሚወጡ ደረጃዎች ስራ ላይ እንዲውሉ መደረጉ የሕብረተሰቡን ጤንነትና ደሕንነት ከማስጠበቅ ባሻገር የንግድ ስርዓትና ውድድሩም ፍትሐዊ አንዲሆን ያደርጋል ብለዋል። የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ እንዳለው መኮንን በበኩላቸው በአገሪቱ  ደረጃዎችን የሚያወጡና የሚያስፈጽሙ አካላት በቅንጅት መስራት ይገባቸዋል። በተለይም በአግባቡ ቁጥጥር ሊደረግባቸው የሚገቡ አስገዳጅ ደረጃዎችን ስራ ላይ በማዋል የሕብረተሰቡን ደሕንነት መጠበቅ እንደሚያስፈልግ ነው አቶ ይልማ የተናገሩት።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም