በክረምት ወራት የተጀመረው የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ተግባር በበጋው ወራትም ተጠናክሮ ይቀጥላል

67
አዲስ አበባ ነሀሴ 22/2010 በአዲስ አበባ አቅመ ደካሞችን በመርዳት በክረምት ወራት የተጀመረው የበጎ አድራጎት ተግባር  በበጋው ወቅትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገለፀ። የቦሌ ከፍለ ከተማ አስተዳደር የበጎ አድራጎት አገልገሎት የሚሰጡ ወጣቶችን በማስተባበር የ15 አባወራና እማወራ የፈረሱ ቤቶች እድሳት በማካሄድ ላይ ይገኛል። ይህ የበጎ አድራጎት ተግባር የሚካሄደው በይቅርታና መደመር መርህ በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሂደት መሰረት በማድረግ መሆኑን የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ፍቅሬ ተናግረዋል። ይህ በአዲስ አበባ ከተማ በጎ ፍቃደኛ ወጣቶች እየተከናወነ ያለው የአቅመ ደካሞችን መኖሪያ ቤቶች ማደስ መርሃ-ግብር በበጋው ወራትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይደረጋል ብለዋል። "ቦሌ ድጋፍ የሚሹ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩበት አይደለም" የሚለው ተለምዷዊ አስተሳሰብ የተሳሳተ መሆኑን የጠቆሙት ዋና ሥራ አስፈፃሚው በአካባቢው ድጋፍ ሊደረግላቸው የሚገባ በርካቶች መኖራቸውን ጠቅሰዋል። በመሆኑም በአካባቢው ያሉ ባለሃብቶችን፣ ታዋቂ ከያኒያንንና አትሌቶችን በማስተባበር  የአቅመ ደካሞችን ቤት የማደስ ተግባር በመከናወን ላይ ነው ብለዋል። ይህን በጎ ተግባር በመፈፀምም እነዚህ የህብረተሰብ ክፍሎች በአዲስ ዓመት ተደስተው ያሳልፉ ዘንድ የተለያዩ መሰል ተግባራት በመከናወን ላይ መሆኑንም አመልክተዋል። በቀጣይም መብራትና ውሃ የሌላቸው ቤቶች እንዲያገኙና በዘላቂነት የሚረዱበት መንገድ አንዲበጅ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑም ጠቁመዋል። በዛሬው እለት የማብሰያና የመጸዳጃ ቤቶቻቸው ከታደሱላቸው አቅመ ደካሞች መካከል ወይዘሮ አይሻ ብሬ በሰጡት አስተያየት ደጋፊ  በማጣታቸው ላለፉት ዓመታት በከፍተኛ ችግር ህይወታቸውን ሲገፉ መኖራቸውን ገልፀዋል። በማብሰያና መፀዳጃ ቤት እጦት ሳቢያ በየጎረቤቱ ይንከራተቱ እንደነበር የሚናገሩት ወይዘሮዋ በዛሬው እለት የተደረገላቸው ድጋፍ የቆየ ችግራቸውን አንደሚፈታላቸው ተናግረዋል። ይህ እውን እንዲሆን ለተጉት መንግስትና የበጎ አድራጎት ወጣቶች ምስጋና አቅርበዋል። ይህ መሰል ድጋፍ ሌሎች ጧሪ፣ ደጋፊና አይዞህ ባይ ላጡ ዜጎችም እንዲዳረስ ጠይቀዋል። የበጎ አድራጎት ተግባሩ አስተባበሪ ወጣት ዘሪሁን ከበደ በበኩሉ ወጣቶቹ አቅመ ደካሞችን በመጠየቅና በመንከባበክ ዘንድሮ የተጀመረው የቤት ማደስ ተግባር በበጋው ወቅትም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጿል። ወጣቶቹ ለሚያከናውኑት የበጎ አድራጎት ተግባር ድጋፍ እያደረጉ ያሉ ወገኖችን አመስግኖ በቀጣይም ለበጎ አድራጎት ተግባሩ የሚያስፈልጉ የቁሳቁስ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል። በክፍለ ከተማው ከ100ሺህ በላይ ወጣቶች በተለያዩ የበጎ አድራጎት ዘርፎች ተደራጅተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ከክፍለ ከተማው የተገኘው መረጃም ይጠቁማል። ዛሬ በተጀመረው የቤት እድሳት መርሃ ግብር  መሰረት በክፍለ ከተማው 15 ወረዳዎች የተመረጡ 15 ቤቶች እድሳት እስከ ነሐሴ 24 ቀን 2010 ዓ.ም ድረሰ ይከናወናል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በአዲስ አበባ ከተማ በእድሜ የገፉና አቅመ ደካማ የህብረተሰብ ክፍሎችን መኖሪያ ቤቶች  ለማደስ የታቀደውን መርሃ-ግብር በይፋ ባለፈው እሁድ ማስጀመራቸው ይታወሳል። ከከተማ አስተዳደሩ በተገኘው መረጃ መሰረት ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተገኙበትን ጨምሮ በጠቅላላው 114 መኖሪያ ቤቶች ዕድሳት ይደረግላቸዋል።              
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም