በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሀት የወደሙ ጤና ተቋማትን ስራ ለማስጀመር የሚረዳ የሕክምና ቁሳቁስና መድኃኒት ድጋፍ ተደረገ

84

ባህር ዳር ታህሳስ 28/2014 (ኢዜአ) ሁለት ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በአማራ ክልል በአሸባሪው የህወሃት ወራሪ ሀይል የወደሙ ጤና ተቋማትን ስራ ለማስጀመር የሚረዳ ከ718 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው የሕክምና ቁሳቁስና መድኃኒት ድጋፍ አደረጉ።

ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች በጦርነቱ ለተጎዱ ወገኖች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንዲያጠናክሩ ተጠይቋል።

''ዶክተርስ ዊዝ አፍሪካ ኩዋም'' እና ከ''እዩ ኢትዮጵያ'' የተሰኙ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች በተወካዮቻቸው አማካኝነት ድጋፉን ለክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ አስረክበዋል።

''የዶክተርስ ዊዝ አፍሪካ ኩዋም'' ፕሮግራም ኃላፊ ዶክተር አደመ ፀጋዬ በወቅቱ እንደገለጹት ድርጅታቸው  ድጋፉን ያደረገው በወረራው የተጎዱ ጤና ተቋማትን መልሶ ሥራ ለማስጀመር የሚደረገውን ሂደት ለማገዝ ነው።

''ድጋፉን ዛሬ ጀመርን እንጂ፤ የመጨረሻችን አይደለም'' ብለዋል።

የእዩ ኢትዮጵያ ፕሮግራም ኦፊሰር አቶ መልካሙ ወንዱ በበኩላቸው ወራሪው ሀይል በጤና ተቋማት ላይ ባደረሰው ውድመት የገጠመውን ችግር ለማቃለል ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል።

የኢፌዴሪ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ፋሲካው ሞላ ድርጅቶቹ በጤና ተቋማቱ ላደረጉት ድጋፍ አመስግነዋል።

ሁሉም ሲቪክ ማህበረሰብ ድርጅቶች በአማራና አፋር ክልሎች የወደሙ መሰረተ ልማቶችን መልሶ በመገንባትና በማቋቋም ሂደት ሚናቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል።

"መላ ኢትዮጵያዊያን በመተባበር በክልሎቹ የተፈጸመን ወረራ እንደቀለበሱ ሁሉ የወደሙ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ሂደት መረባረብ ይገባል" ብለዋል።

የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶክተር መልካሙ አብቴ በበኩላቸው በአሸባሪው የወደሙ ጤና ተቋማትን ወደቀደመ ቁመናቸው ለመመለስ የሁሉም አካላት ርብርብና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አመልክተዋል።

ድርጅቶቹ ያደረጉት ድጋፍ ጉዳት ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት ጥቅም ላይ እንደሚውል አረጋግጠዋል።

ሌሎች ድርጅቶችም የወደሙ ጤና ተቋማትን መልሶ ለመገንባት በሚደረገው ጥረት የጀመሩትን ድጋፍ  እንዲያጠናክሩ ኃላፊው ጠይቀዋል።

የጤና ሚኒስትር ዶክተር ሊያ ታደሰ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ  አሸባሪው ህወሓት በከፈተው ጦርነት በአፋርና አማራ ከ2ሺህ 700 በላይ የጤና ተቋማት ጉዳት እንደደረሰባቸውና ከነዚህም 42ቱ ሆስፒታሎች መሆናቸውን ማስታወቃቸው ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም