የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በመዲናዋ ለአቅመ ደካማ ዜጎች ያስገነባቸውን 59 የመኖሪያ እና 30 የንግድ ቤቶች ለተጠቃሚዎች አስረከበ

66

ታህሳስ 28/2014/ኢዜአ/ የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በመዲናዋ ለአቅመ ደካማ ዜጎች ያስገነባቸውን 59 የመኖሪያ እና 30 የንግድ ቤቶች ለተጠቃሚዎች አስረከበ፡፡

ቤቶቹ የተገነቡት የቀድሞ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በስሩ የሚገኙ ተጠሪ ተቋማትንና ባለሃብቶችን በማስተባበር ሲሆን፤ ግንባታውም የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የበጎ አገልግሎት ጥሪን ተከትሎ መጀመሩ ተገልጿል፡፡

የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ አቶ መላኩ አለበል በዛሬው እለት የቤቶቹን ቁልፍ ለተጠቃሚዎች አስረክበዋል፡፡

ሚኒስትሩ በዚህን ወቅት እንዳሉት፤ ቤቶቹን በመገንባት ረገድ በጎ ፈቃደኛ ባለሃብቶች ከፍተኛ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

በዚህም 25 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በሆነ ወጪ 59 መኖሪያ እና 30 ንግድ ቤቶችን ገንብቶ ማስረከብ መቻሉን አስረድተዋል፡፡

ሚኒስቴሩ በተጨማሪም በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን ከራት ከተማ  አንድ ብሎክ ትምህርት ቤት እየገነባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ይህም ከተባበረን በርካታ ችግሮችን መፍታት እንደምንችል ያመላከተ ነው ብለዋል፡፡

የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ የሆኑ ግለሰቦች በበኩላቸው ከመኖሪያ ቤት በተጨማሪ ገቢ ለማግኘት የሚያስችል ስልጠና እና ሌሎች ድጋፎች እንደተደረጉላቸው ተናግረዋል፡፡

ሚኒስቴሩ ያከናወነው በጎ ተግባር የዘመናት ችግራቸውን የፈታ መሆኑን ገልጸው፤ ለተደረገላቸው በጎ ተግባር ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በተጨማሪም በርክክብ መርሃ-ግብሩ ላይ የቤት ተጠቃሚ ለሆኑ አቅመ ደካማ ዜጎች የበዓል መዋያ የገንዘብ ስጦታ ተበርክቶላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም