በዞኑ 32 ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለ የተፋሰስ ልማት ስራ ተጀመረ

91

ነገሌ ታህሳስ 28.2014( ኢዜአ) በምእራብ ጉጂ ዞን 32ሺህ ሄክታር መሬት ያካለለ የበጋ ወቅት የተፋሰስ ልማት ስራ ዛሬ ተጀመረ።

በዞን ደረጃ የሚካሄደው የዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ስራ በገላና ወረዳ በይፋ ተጀምሯል፡፡

የዞኑ ግብርና  ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አያኖ ዓለማየሁ በወቅቱ እንደተናገሩት በበጋ ወቅት 167 ተፋሰሶችን መሠረት ያደረጉ የአፈርና ወሀ ጥበቃ ስራዎች ይከናወናሉ፡፡

በዘጠኝ ወረዳዎች በሚካሄደው የተፋሰስ ልማት ስራ 215 ሺህ 500 ሕዝብ እንደሚሳተፍ ተናግረዋል ።

በልማቱ ከሚሳተፉ መካከል 35 ሺህዎቹ ሴቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

የተፋሰስ ልማት ስራው ለተከታታይ 60 ቀን የሚቆይ መሆኑን ጠቁመው ለስራው የሚያገለግሉ ዶማና አካፋን ጨምሮ ሌሎችም የነፍስ ወከፍ የእጅ መሣሪያዎች መቅረባቸውን አመልክተዋል፡፡

በተፋሰስ ልማት ስራው ከሚከናወኑት ተግባራት የማሳና የተራራ ላይ እርከን ፣ የምንጭ ማጎልበት፣  የተጎዳ የግጦሽ መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ መከለል ዋናዎቹ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የአፈር ለምነትን መጠበቅ፣ የአካባቢ መራቆትንና የድርቅ ተጋላጭነትን መቀነስ እንዲሁም አረንጓዴ ልማትን ማስፋፋት በመርሀ ግብሩ በግብነት መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡

በዞኑ በመጪው ክረምት ለሚካሄደው የአረንጓዴ ዐሻራ መርሐ ግብር እስካሁን ከ10 ሚሊዮን በላይ ችግኞች መዘጋጀታቸውን ምክትል ኃላፊው  አስታውቀዋል፡፡

በገላና ወረዳ የዋጩ ቀበሌ ነዋሪ አቶ ጥላሁን ሹና ከዚህ ቀደም የአካባቢያቸው የደን ይዞታ  የተመናመነ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡

ባለፉት አመታት በተከናወኑ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች የደን ይዞታዎች እያገገሙ መምጣታቸውን  ገልጸዋል፡፡

"በተፋሰስ ልማት ስራ በመሳተፍ የተገኘውን ለውጥ በማስቀጠል ተጠቃሚ ለመሆን አካባቢዬን ለማልማት ዝግጁ ነኝ "ብለዋል፡፡

ሌላዋ ወይዘሮ አበበች ዱቤ በበኩላቸው የተፋሰስ ልማት ስራ ከተጀመረ ወዲህ በአካባቢው የእንስሳት መኖ አቅርቦት እጥረት እየተቃለለ መምጣቱን  አመልክተዋል።

"በአካባቢ መራቆት ሳቢያ ድርቅ እንዳይከሰት በልማት ስራው ከመሳተፍ ሌላ ምርጫ የለንም" ብለዋል፡፡

"ባለፉት ዓመታት የተካሄደ የተፋሰስ ልማት ስራ ለከብቶቻችን ሳር ለማቅረብ አስችሎናል" ያለው ደግሞ የቀበሌው ነዋሪ ወጣት ታምሩ ደመዮ ነው፡፡

ህብረተሰቡ ካለፉት ዓመታት ተሞክሮ በመነሳት በዘንድሮ የተፋሰስ ልማት ስራ የመሳተፍ ተነሳሽነቱ መጨመሩን ወጣት ታምሩ ተናግሯል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም