ሕዝበ ክርሰቲያኑ የገና በዓልን ሲያከብር የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ

92

ታህሳስ 28/2014/ኢዜአ/  ሕዝበ ክርሰቲያኑ የኢየሱስ ክርስቶስን የልደት በዓልን ሲያከብር የተፈናቀሉ ወገኖችን በመደገፍና ጉዳት የደረሰባቸውን ሐዘናቸውን በመካፈል ሊሆን እንደሚገባ የኃይማኖት አባቶች ጥሪ አቀረቡ። ኢትዮጵያዊያን ለአገራቸው ሰላም በአንድነት ሊቆሙ እንደሚገባም ነው ያስገነዘቡት፡፡

የኃይማኖት አባቶቹ የገና በዓልን ምክንያት በማድረግ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብጹዕ አቡነ ማትያስ ምዕምኑ በዓሉን ሲያከብር የተፈናቀሉ ወገኖችን በማሰብ እንዲሆን ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

በዓሉን ስናከበር የተራበውን በማብላት፣ የተጠማውን በማጠጣት፣ የታረዘውን በማልበስ እንዲሁም የታመመውንና የታሰረውን በመጠየቅ ሊሆን ይገባል ነው ያሉት።

በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ካርዲናል ብርሃነየሱስ ሱራፌል በበኩላቸው፤ የኢየሱስ ክርስቶስ የልደት  በዓልን ስናከብር በጦርነቱ የተፈናቀሉትንና ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች በማሰብና ሐዘናቸውን በመካፈል ሊሆን ይገባል ብለዋል።

እያንዳንዱ ሰው ወንድምና እህቱን እንደራሱ አድርጎ እንዲወድ ታዟል ያሉት ካርዲናል ብርሃነየሱስ፤ የሰላምን ሰንሰለት ከሚበጥሱት ከትዕቢት፣ ከጥላቻ፣ ከኩራትና ከቁጣ መንፈስ መራቅ እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ወንጌል አማኞች አብያተ ክርስቲያናት ካውንስል ጠቅላይ ጸሐፊ ቄስ ደረጀ ጀምበሩ በበኩላቸው፤ የገና በዓልን አለን ያሉትና ተስፋ ያደረጉት ንብረት ወድሞና ተዘርፎ ቤተሰቦቻቸውን አጥተው በሀዘን ላሉ ወገኖቻችን ፍቅርና አብሮነትን በሚያሳይ መልኩ ማክበር ይገባል ብለዋል።  

ስለ ሰላም ማስተማርና መልካም ምሳሌ ሆኖ መገኘት ከክርስቲያኖች የሚጠበቅ በመሆኑ ምዕመናን ራሳቸው ታርቀው የማስታረቅ አገልግሎታቸውን እንዲያከናውኑ ጥሪ አቅርበዋል።

በኢትዮጵያ አስተማማኝና ዘላቂ ሰላም ለማስፈን ተቀራርበን መሥራት ይገባናል ያሉት ቄስ ደረጀ፤ በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ አገር ያሉ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት መቆም እንዳለባቸው ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም