የገና በዓልን የምናከብረው ከተቸገሩ ወገኖቻችን ጋር በጋራ በመሆን ነው

80

ታህሳስ 28/2014/ ኢዜአ/ የገና በዓልን በችግር ውስጥ ከሚገኙ ወገኖች ጋር በጋራ በመሆን እንደሚያከብሩ ኢዜአ ያነጋገራቸው ወደ አገር ቤት የመጡ ዳያስፖራዎች ገለጹ፡፡

ዳያስፖራው የበዓል ስጦታውን ለተቸገሩ ወገኖች እንዲያበረክትም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
 

አሸባሪው የሕወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልሎች ወረራ በፈጸመባቸው አካባቢዎች በሰላማዊ ዜጎች ላይ ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት ፈጽሟል፡፡

የሽብር ቡድኑ ንጹሃን በአሰቃቂ ሁኔታ በመጨፍጨፍ፣ ሴቶችን አስገድዶ በመድፈር፣ የግለሰብ ቤቶችና የአገልግሎት ተቋማትን በማውደምና በመዝረፍ ለህዝብ ያለውን ጥላቻ በተግባር አሳይቷል፡፡

በዚህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን ጥሪ ተቀብለው ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ዳያስፖራዎች ለወደሙ የጤና ተቋማት የሚሆን የህክምና ቁሳቁስ ይዞ ከመምጣት ጀምሮ በችግር ወስጥ የሚገኙ ወገኖችን እያገዙ ይገኛሉ፡፡

ኢዜአ ያነጋገራቸው በኔዘርላንድ አምስተርዳም ነዋሪ ወጣት ናኦል አመንቴ፣ ወይዘሮ ራሔል ዳልተን ከአየርንድ ደብሊን እና ወይዘሮ ሐረገወይን ከበደ ከኔዘርላንድ ሮተርዳም እንደሚሉት፤ በዓሉን በአሸባሪው ህወሃት ወረራ በችግር ውስጥ ከሚገኙ ወገኖች ጋር ማክበር ይገባል፡፡

ከዚህ አኳያ በዓሉን ለተጎዱ ወገኖችን ምሳ ማብላት፣ማበረታታትና ስጦታዎችን በመስጠት እንደሚያከብሩ ነው የጠቆሙት፡፡

ገና የሚታወቀው ስጦታ በመስጠት እንደሆነ የሚገልጹት ዳያስፖራዎቹ፤ የዘንድሮውን የበዓል ስጦታ ለተቸገሩ ወገኖች ማድረግ ይገባል ነው ያሉት፡፡  

የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላቱ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የገና በዓል የሰላምና የፍቅር እንዲሆንም መልካም ምኞታቸውን ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም