ለጸጥታ አካላት ለገና በዓል የእርድ እንስሳት ድጋፍ ተደረገ

60

መተማ፣ ታህሳስ 28 ቀን 2014 (ኢዜአ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ህዝብ ለጸጥታ አካላት ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ለገና በዓል መዋያ የእርድ እንስሳትን ድጋፍ አደረገ።

በድጋፍ አሰጣጡ ሥነ-ሥርዓት ላይ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው እንደተናገሩት፤ የእርድ እንስሳት ድጋፍ የተደረገው ሠራዊቱ በዓሉን ቤታቸው ሆነው ያከበሩ ያህል እንዲሰማቸው ለማድረግ ነው።

በዚህም የዞኑ ነዋሪዎች 78 ሠንጋዎችን፣ 54 በጎች እና ፍየሎችን ዛሬ ለሠራዊቱ አስረክበዋል።

ድጋፉ የተደረገው በዞኑ ለሚገኙ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ጨምሮ ለተለያዩ የጸጥታ አካላት መሆኑን ገልጸዋል።

የጸጥታ አካላቱ ጠላትን በመመከትና ትልልቅ ጀብዱ በመፈጸም ህዝቡ እፎይታ እንዲያገኝ ማድረጋቸውንም አመልክተዋል።

ሠራዊቱን ወክለው ድጋፉን የተረከቡት አባላት ህዝቡ ያደረገው ድጋፍ ሠራዊቱ እየተወጣ ያለውን ግዳጅ የበለጠ ለማጠናከር እንደሚያያገዝ ተናግረዋል።

"ህዝቡ ከህግ ማስከበሩ ጀምሮ ያልተቋረጠ ድጋፍ ማድረጉ የሚያስመሰግን ተግባር ነው" ብለዋል።

የህዝቡ ድጋፍ ሠራዊቱ ግዳጁን እንዲወጣ ወኔና ስንቅ እንደሚሆነው ገልጸው፤ ሠራዊቱ ደከመኝ ሳይል ውጤታማ መሆኑን ገልጸዋል።

በቀጣይ ማንኛውንም የጠላት እንቅስቃሴ በአስተማማኝ ሁኔታ በመመከት ህዝብና መንግስት የጣለባቸውን  ታሪካዊ ሃላፊነት በብቃት እንደሚወጡም አስታውቀዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም