አርቲስት ዓለምጸሃይ አዲስ አበባ ገባች

100
አዲስ አበባ ነሐሴ 22/2010 አርቲስት ዓለምፀሀይ ወዳጆ አዲስ አበባ ገባች። አርቲስቷ ቦሌ አለም አቀፍ አየረ ማረፊያ ስትደርስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ መለስ አለም እንዲሁም የአዲስ አበባ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ረዳት ፕሮፌሰር ነብዩ ባዬ አቀባበል አድርገውላታል። በርካታ አርቲስቶችም አቀባበል ለማድረግ በስፍራው ተገኝተዋል። የአርቲስቷን መምጣት በማስመልከት በብሄራዊ ትያትር ቤት መግለጫ እንደሚሰጥ የተገለፀ ሲሆን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ውይይት ታደርጋለች ተብሎ ይጠበቃል። ከአርቲስት ዓለምፀሀይ በተጨማሪ አርቲስት አበበ በለውም በዛሬው እለት ወደአገሩ ተመልሷል። አርቲስት ዓለምጸሃይ ወዳጆ ወደ አሜሪካ ካቀናች በኋላ ቤተሰቧን ለማስተዳደር በርካታ ስራ የሰራች ቢሆንም በዚህ ሁኔታ ውስጥም ሆና ከሙያዋ ባለመለየቷ እድሜ ዘመኗን በሙሉ በኪነ-ጥበብ ውስጥ በተዋናይነትና በገጣሚነት አሳልፋለች። “ጥበብ ለእኔ እንደሱስ ነው፤ ከሱ ተለይቼ መኖር አልችልም'' የምትለው አለምጸሃይ ወዳጆ በርካታ ታዋቂ ድምጻውያን ያዜሟቸውን ግጥሞች በመድረስ ትታወቃለች። በሙዚቃ አስተማሪዋ መላኩ አሻግሬ አማካኝነት በአገር ፍቅር ቲያትር መድረክ ላይ የመተወን ዕድል ተመቻችቶላት የአማተር ክበብ አባል በመሆን ወደ ኪነጥበቡ ዓለም ተቀላቅላ እስካሁን ድረስ ለዘርፉ ዘመን የማይሽራቸውን ስራዎቿን እያበረከተች ትገኛለች። ዓለምጸሀይ በ18 ዓመቷ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ በብሔራዊ ትያትር ለሁለት ዓመታት የተሰጠውን ስልጠና በመከታተል በዚያው ትያትር ቤት በከፍተኛ ተዋናይነት ተቀጥራ ለ17 አመታት በተዋናይነትና በጸሃፊነት አገልግላለች። በዚህ ጊዜ ውስጥ በተዋናይነት በቬኑሱ ነጋዴ፣ ሐምሌትና ዋናው ተቆጣጣሪ በተሰኙ ከውጭ ቋንቋ ተተርጉመው በተዘጋጁ ትያትሮች ላይ በመተወን ከፍተኛ የሆነ ተወዳጅነትን ያተረፈች አርቲስት ናት። የኢትዮጵያ ተዋናዮችን ማህበር መስራች አባል ከመሆን ባለፈም በምክትል ሊቀመንበርነት ለ14 ዓመታት በማገልገል የተዋናዮች ደመወዝ እንዲሻሻል ስኬታማ ቅስቀሳ ማድረግ ችላለች። 'በሩ' በሚል ርዕስ የጻፈችው ትያትር በራስ ቲያትር እየታየ ከነበረበት መንግስትን የሚተች ዓይነት በመሆኑ አንዳንድ ማሻሻያዎችን እንድታደርግበት በማስታወቂያ ሚኒስትሩ በኩል ትዕዛዝ ተሰጥቷት ባለመቀበሏ ትያትሩ እንዳይታይ ታግዷል። በ1992 ዓ ም ጣይቱ የባህል ማዕከልን በዋሽንግተን ዲሲ ማቋቋም መቻሏ የኪነጥበብ ስራዋን በስፋት ለመስራት ዕድል ማግኘቷን ትናገራለች።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም