የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል እድሳት ሊደረግለት ነው

170

ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) ከ90 ዓመታት በላይ አገልግሎት ሲሰጥ የቆየው የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል እድሳት ሊደረግለት መሆኑን የካቴድራሉ የእድሳት ኮሚቴ አስታወቀ፡፡

የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴድራል በንጉሰ ነገስት አጼ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግስት በ1922 ዓ.ም የተገነባ ሲሆን ከ90 ዓመት በላይ አገልግሎት ሰጥቷል፡፡

የእድሳት ኮሚቴው ዛሬ በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው፤ ካቴድራሉ በአሁኑ ወቅት የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ስለደረሰበት እድሳት ያስፈልገዋል።

ካቴደራሉ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ባለፈ የአገር ቅርስ በመሆኑ ይዘቱንና ቅርሱን ጠብቆ ለማደስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን የእድሳቱ ገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ቀሲስ ዶክተር ብሩክ ሞላልኝ ተናግረዋል ።

በዚህም ጥር 7 ቀን 2014 ዓ.ም ዓመታዊ ክብረ በዓሉ ከተከበረ በኋላ ታቦተ ህጉ ወደ በዓለወልድ ቤተ ክርስቲያን እንደሚዘዋወር ገልጸዋል።

ለእድሳቱ ዓለም አቀፍ ጨረታ እንደሚወጣና ከቅርስ ጥበቃ ባለሙያዎች ጋር በመሆን እድሳቱ እንደሚጀምር ኮሚቴው አስታዉቋል።

በመሆኑም በአገር ውስጥና ከአገር ውጭ የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች ለህንጻው እድሳት የተለመደውን ትብብርና ድጋፍ እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ስላሴ ካቴደራል ፖትርያርኮች እና የሊቃነ ጳጳሳት በዓለ ሲመት የሚከናወንበትና በመካነ እረፍታቸው ጊዜም የማረፊያ ቦታ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ካቴድራሉ ለአገር ከፍተኛ አስተዋጾ ያደረጉ ግለሰቦችና መሪዎች መካነ መቃብር የሚገኝበት ሲሆን፤ በውስጡም ዘመናትን ያስቆጠሩ ቅርሶችን ይዟል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም