መንግስታዊ አገልግሎትን በተቀላጠፈ መንገድ መስጠት ለአገራዊ ሰላም ግንባታ ጉልህ ሚና አለው

103

ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) መንግስታዊ አገልግሎትን ለህብረተሰቡ በተቀላጠፈ መንገድ መስጠት ለአገራዊ ሰላም ግንባታ ጉልህ ሚና እንዳለው የሰላም ሚኒስቴር ገለጸ፡፡

ሚኒስቴሩ ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመተባበር "ሰላማዊ ሠራተኛ ለዜጎች አገልግሎት እርካታ" በሚል መሪ ሃሳብ የምክክር መድረክ ያካሄደ ሲሆን፤ ከክልልና ዞን የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የመጡ አመራሮች ተሳትፈዋል፡፡

በመድረኩ "የኢትዮጵያ የሰላም ፖሊሲ እና የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ሚና"፣ "የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የሰላም ግንባታ ማካተቻ ማንዋል" እንዲሁም "የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት የምክክር መድረክ ሂደት ስታንዳርድ" በሚሉ ጉዳዮች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡

የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ታዬ ደንደአ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ ከለውጡ በፊት በነበሩ ጊዜያት ኢትዮጵያ ከገጠሟት ስብራቶች መካከል የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት በአገልግሎት አሠጣጥ መዳከም አንዱ ነው።

ይህም በአገራዊ ሰላምና መግባባት ላይ እንቅፋት ከመፍጠሩም በላይ ማገልገልን ባህል በማድረግ ረገድ እንቅፋት ፈጥሮ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

በመሆኑም የሰላም ሚኒስቴር ከሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን ጋር በመሆን የተቀላጠፈ አገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር እየሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ለአገራዊ ሰላም ግንባታ ፋይዳው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም የሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ራሳቸውን ከብልሹ አሰራር አጽድተው ሰላማዊ፣ ግልጽና ተጠያቂነት ያለው አሰራር እንዲዘረጉ አስገንዝበዋል፡፡

ይህም ለሰላምና ብሔራዊ መግባባት ካለው ፋይዳ ባሻገር ለአገራዊ ልማት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ጠቁመዋል፡፡

በፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽን የኮሚሽነሩ አማካሪ መስፍን በረታ በበኩላቸው ኮሚሽኑ ለህዝብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት አሰጣጥ ለሰላም መስፈን ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ከዚህ አኳያ በየደረጃው ያለው ሰራተኛ የተሰጠውን ኃላፊነት አክብሮ የተቀላጠፈ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት በሲቪል ሰርቪስ ተቋማት ላይ የሚስተዋለው ፍትሃዊ ያልሆነ አሰራር እንዲቀረፍ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ ጠይቀዋል፡፡

በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች ስር የሰደዱ በመሆናቸው ጥናትን መሰረት ያደረገ መፍትሄ መስጠት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም