ህብረተሰቡ እያደረገልን ያለው ወገናዊ ድጋፍ ብርታት ሆኖናል-የዘማች ቤተሰቦች

89

ጎንደር፤ ታህሳስ 27/2014 (ኢዜአ) ህብረተሰቡ እያደረገልን ያለው ያልተቋረጠ ወገናዊ ድጋፍ ብርታት ሆኖናል ሲሉ በጎንደር ከተማ የዘማች ቤተሰቦች ተናገሩ፡

በከተማው የሚገኙ ባለሀብቶችና የንግዱ ማህብረሰብ አባላት ለዘማች ቤተሰቦች ለገና በዓል መዋያ ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ስጦታ በትናንትናው ዕለት  አበርክተዋል፡፡  

የዘማች ቤተሰብ የሆኑት ወይዘሮ ደሳለች አያናው ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት  ’’ሀገር ስትወረር ቆሜ አላይም ብሎ አራት ልጆቹን ትቶ በግምባር የዘመተው ባለቤቴ ከሄደ ጀምሮ የህዝቡ ድጋፍና እንክብካቤ አልተለየኝም’’ ብለዋል፡፡

ባለቤታቸው ለሀገርና ህዝብ ሲሉ በመዝመታቸው ኩራት እንደተሰማቸው የገለጹት ወይዘሮ ደሳለች፤ለገና በዓል መዋያ የንግዱ ማህብረሰብ አባላት ላደረጉላቸው የ5 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

''ባለቤቴ ወደ ግንባር ከዘመተበት  ጊዜ ጀምሮ  ህዝቡ የበዓል መወያ ገንዘብና የእርድ እንስሳት በመስጠት ከጎኔ መቆሙ ብርታት ሆኖኛል'' ያሉት ደግም ወይዘሮ ወርቄ አስፋው ናቸው፡፡

’’ባለቤቴ ከጎኔ ሲለየኝ ጭንቀትና ፍርሃት አድሮብኝ ነበር’’ ያሉት ወይዘሮዋ የህዝቡ ያልተቋረጠ ድጋፍና እንክብካቤ ብርታት ሆኗቸው ልጆቻቸውን ያለስጋት እያሳደጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ለበዓል መዋያ ለተደረገላቸው የ5 ሺህ ብር የገንዘብ ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

የጃንተከል ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሆነአለም አሻግሬ ለገና በዓል መዋያ ’’አንድ በግ ለአንድ የዘማች ቤተሰብ’’ በሚል ከሩብ ሚሊዮን ብር በላይ ገንዘብ ከባለሀብቶችና ነጋዴዎች መሰብሰቡን ጠቁመዋል።

በክፍለ ከተማው ለሚገኙ 50 የዘማች ቤተሰቦች ለእያንዳንዳቸው 5 ሺህ ብር ለበዓል መዋያ ድጋፍ መደረጉን አስረድተዋል።  

የተደረገው ድጋፍ ለወገናቸውና ለሀገራቸው ሲሉ ግንባር ለሄዱ ዘማች ቤተሰቦች  ብርታት እንደሆነ አመልክተዋል።  

የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ባዩህ አቡሃይ በበኩላቸው የከተማው የንግድ ማህብረሰብ አባላት ለዘማች ቤተሰቦች ያልተቋረጠ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።

የከተማው ህዝብ ለህልውና ዘመቻው የስንቅ ዝግጅት ከማድረግ ጀምሮ ህዝባዊ ደጀንነቱን በተግባር በማረጋገጥ ድሉ እንዲጠናከር ያበረከተው አስተዋጽኦ ዋጋ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል።

የንግዱ ማህብረሰብ ለዘማች ቤተሰቦች ላደረጉት የገንዘብ ስጦታ ያመሰገኑት ምክትል ከንቲባው፤ድጋፉ ለህዝባዊ ወገንተኝነቱ ማሳያ  መሆኑን ተናግረዋል።

ለዘማች ቤተሰቦች እየተደረገ ያለው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም