ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት በነጻ ህሊና እና ልብ አገሬን በቅርበት ለማየትና የድርሻዬን ለመወጣት ነው

74

ታህሳስ 27 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት በነጻ ህሊና እና ልብ አገሬን በቅርበት ለማየትና የድርሻዬን ለመወጣት ነው" ስትል ጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ ገለጸች።

በአሜሪካን አገር በሚገኘው ሲ.ቢ.ኤስ ውስጥ የምትሰራው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ጋዜጠኛ ሔርሜላ አረጋዊ ዛሬ ማለዳ አዲስ አበባ ገብታለች።

ጋዜጠኛ ሔርሜላ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ስትደርስም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች፣ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴና ሌሎችም አቀባበል አድርገውላታል።

አሸባሪው ሕወሓት በፌዴራል መንግስት ላይ ጦርነት መክፈቱን ተከትሎ ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የሚያራምዱትን አቋም በጽኑ በማውገዝ ትግል እያደረገች የምትገኘው ጋዜጠኛ ሔርሜላ፤ አንዳንድ የምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ኢትዮጵያን በሚመለከት የሚሰሩት ዘገባ እውነታን የካደ በመሆኑ በይፋ ስትቃወም ቆይታለች።

የኢትዮጵያ የዲያስፖራ ማሕበረሰብ አባላትና የኢትዮጵያ ወዳጆች የተሳተፉበት የ'በቃ' እንቅስቃሴ ውስጥም ጉልህ ሚና ነበራት።

ጋዜጠኛ ሔርሜላ አዲስ አባበ ስትደርስ ''የምወዳትን አገሬን በማየቴ ደስ ብሎኛል፤ ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት በነጻ ህሊና እና ልብ አገሬን በቅርበት ለማየትና የድርሻዬን ለመወጣት ነው" ብላለች።

ጋዜጠኛዋ አዲስ አበባ ስትደረስ የሚያስደስት አቀባበል እንደተደረገላት ገልጻለች።

ጋዜጠኛ ሔርሜላን በቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ በመገኘት አቀባበል ያደረጉላት በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጀነራል አምባሳደር ዶክተር ገበየሁ ጋንጋ ''በመምጣትሽ ደስ ብሎናል'' ብለዋል።

የጋዜጠኛ ሄርሜላ የአገር ቤት ቆይታም መልካም እንደሚሆን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም