"በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘርን ማንኛውንም የውጭ ጫና አፍሪካውያን በጋራ መመከት አለብን"

49

ታህሳስ 27/2014/ኢዜአ/ በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘርን ማንኛውንም የውጭ ጫና አፍሪካውያን በጋራ መመከት አለብን ሲል ደቡብ አፍሪካዊው የማህበረሰብ ንቅናቄ መሪ ሎንታታ ላክስ ገለጸ።

ሎንታታ ላክስ ደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ሌሎች አፍሪካዊያን ሃብትና ንብረት ላይ ጥፋት እንዳይደርስ ከለላ እየሆነ እንደሚገኝም በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኮሙዩኒቲ አባላት ይናገራሉ።

ደቡብ አፍሪካዊው የማህበረሰብ ንቅናቄ መሪ ሎንታታ ላክስ ዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን አዲስ አበባ ሰላም አይደለችም ውጡ እያሉ የሚያራግቡት ወሬ ፍጹም ሃሰት መሆኑን ከቦታው ማረጋገጥ ችያለሁ ብሏል።

ወደ አዲስ አበባ የመምጣቱ ሚስጥርም በኢትዮጵያ መንግስትና ኢትዮጵያዊያን ላይ እየደረሰ ያለውን የአገር ውስጥና የውጭ ጫና ለመመከት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ እንደሆነም ተናግሯል።

አፍሪካዊያን አንድ ሆነን የሚደርስብንን ጫና መመከት እንደምንችል ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ መልዕክት ለማስተላለፍ አዲስ አበባ መገኘቱን ጠቁሟል።

በቀጣይም በኢትዮጵያ ላይ የሚሰነዘረውን ማንኛውም አይነት ጫና እንደ አፍሪካ ለመመከት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጧል።

እውነታን ከስፍራው ማረጋገጥ እየተቻለ ለአንድ ወገን ያደላ ከእውነት የራቀ የተዛባ መረጃ የሚያሰራጩ አካላትም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ይገባል ብሏል።

ምቹ ቢሮ ውስጥ በመቀመጥ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ሃሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላት ኢትዮጵያን ከመደገፍ ሊያስቆሙኝ አይችሉም ሲል ገልጿል።

በማህበራዊ ትስስር ገጾች "መጤ ጠል ነው" በሚል የሚናፈሰው ወሬም አካውንቱን ጠልፈው የፈጠሩት መሰረተ ቢስ ወሬ መሆኑን ገልጿል።

ኢትዮጵያውያንም የአገራቸውን ሉዓላዊነት የማስጠበቂያ ጊዜ አሁን መሆኑን በመገንዘብ የተከፈተባቸውን የውስጥና የውጭ ጫና በአንድነት ቆመው መመከት እንዳለባቸውም አሳስቧል።

ለአገራቸው መሪ ድጋፍ በመስጠት አንዳንድ ምዕራባውያን የሚያስናዱትን የጥፋት መንገድ በቃ ማለት እንዳለባቸውም ገልጿል።

ኑሯቸውን ደቡብ አፍሪካ በማድረግ ወደ አዲስ አበባ የመጡ ኢትዮጵያዊያንም ስለ ደቡብ አፍሪካዊው የማኅበረሰብ ንቅናቄ መሪ ሎንታታ ላክስ የሚናፈሰው ወሬ የልጁን ለእውነት ዘብ መቆም ያላማከለ መሰረተ ቢስ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ደቡብ አፍሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንና ሌሎች አፍሪካዊያን ሃብትና ንብረት ላይ የሚደርስን ውድመትና ጥፋት በመፋለም ከለላ እያደረገላቸው እንደሚገኝም ምስክርነታቸውን ገልጸዋል።

ሎንታታ ላክስ አንዳንድ ምዕራባዊያን አገራት በኢትዮጵያ ላይ እያደረሱት ያለውን ጫና ለመመከት በተካሄደው የኖሞር  የ''#nomore'' ንቅናቄ በመሳተፍ አፍሪካዊያን ከኢትዮጵያን ጎን እንዲሰለፉ ሲያደርግ የቆየ የኢትዮጵያ ወዳጅ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም