ከተቋም ለተቋም የተጀመረው የመልሶ ማቋቋም ድጋፍ በቤተሰብ ለቤተሰብ ደረጃ ጭምር መተግበር ይገባል

78

ታህሳስ 27/2014/ኢዜአ/ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት ከተቋም ለተቋም የተጀመረው ድጋፍ በቤተሰብ ለቤተሰብ ደረጃ ጭምር መተግበር እንዳለበት የኢኮኖሚ ምሁሩ ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው አለሙ ገለጹ፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን በአማራና አፋር ክልል በከፈተው ጦርነት በርካታ ዜጎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውና የተለያዩ ተቋማት መውደማቸው ይታወቃል፡፡

በፌደራል ደረጃ  የሚገኙ የተለያዩ ተቋማት "አንድ ተቋም ለአንድ ተቋም" በሚል መርህ የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባት እየሰሩ ይገኛሉ፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢኮኖሚክስ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው አለሙ የመልሶ ግንባታ ስራው ለመንግስት ብቻ መተው እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡

አሁን ላይ በተቋማት ለተቋማት የተጀመረው ድጋፍ መሰረታዊ አገልግሎት ሰጭ ተቋማት ወደ መደበኛ ስራቸው እንዲመለሱ አስችሏል ነው ያሉት፡፡

ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ኢኮኖሚያቸው እንዲነቃቃ በማድረግ ረገድም በጎ ሚና እያበረከተ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡

ረዳት ፕሮፌሰሩ አክለውም፤ በተቋማት ለተቋማት የተጀመረው ድጋፍ በቤተሰብ ለቤተሰብ በማስተሳሰር በችግር ውስጥ የሚገኙ ዜጎችን መደገፍ እንደሚገባ መክረዋል፡፡

''ሃምሳ ሎሚ ለአንድ ሰው ሸክሙ ለአምሳ ሰው ግን ጌጡ ነው'' እንዲሉ አንድ ቤተሰብ አንድ ሰው እንዲረዳ በማድረግ የችግሩን ክብደት ማቃለል እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸው አካባቢዎች ጉዳት ካልደረሰባቸው ጋር ሲነጻጸሩ አነስተኛ መሆናቸውን ጠቅሰው፤በመሆኑም ህዝብን ከህዝብ በማስተሳሰር የመልሶ መቋቋሙን ስራ በውጤታማነት ማከናወን ይቻላል ነው ያሉት፡፡

በቤተሰብ ለቤተሰብ ትስስር የሚፈጠረው ድጋፍ  ማህበራዊ መስተጋብርን እንደሚያጎለብትም ገልጸዋል፡፡

በታሪክ የምንታወቅበትን የመረዳዳት ባህል በዚህ ወቅት በመድገም እንደ አገር የገጠመንን ፈተና ተረዳድተን በጋራ መሻገር ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡

ከሞቀ ቤታቸው ወጥተው በችግር ውስጥ የሚገኙ ወገኖችን ወደነበሩበት ህይወት በመመለስ የአሸባሪ ቡድኑን እኩይ ዓላማ ማክሽፍ እንደሚገባም አመልክተዋል፡፡

''መለያየት ሽንፈት መተባበር ግን ድል ነው" ያሉት ረዳት ፕሮፌሰር አጥላው፤ ከተባበርን ችግሩ ከአቅማችን በላይ አይሆንም ብለዋል፡፡

በንብረት ላይ የደረሰው የጉዳት መጠንና በሰዎች ላይ የተፈጸመውን ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ለህብረተሰቡ በማሳወቅ ረገድ ሚዲያዎች የጀመሩትን ስራ አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አመላክተዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም