የባህላዊ እርቅ ሥርዓቶችን በማበልፀግ የሀገሪቱን እድገት ማፋጠን ይገባል

114

ሀዋሳ፣ ታህሳስ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የባህላዊ እርቅ ሥርዓቶችን በጥናትና ምርምር በማጎልበት የሀገርን የብልጽግና ጉዞ ማፋጠን እንደሚገባ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።

''ባህላዊ የእቅር ስርዓታችን ለህብረ ብሄራዊ አንድነታችን'' በሚል መሪ ሀሳብ  ሀገር አቀፍ የውይይት መድረክ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ  ተካሂዷል።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ወርቅነሽ ብሩ የአገር ሽማግሌዎችን የእርቅ ስርዓት ክህሎትን ለመገንባት በየደረጃው ተገቢው ትኩረት ተሰጥቶት ለውጤታማነቱ በቅንጅትና በትጋት የሚሰራበትን አቅጣጫ ለማመላከት መድረኩ መዘጋጀቱን ተናግረዋል።

ባህላዊ የእርቅ ስርዓት የሀገር በቀል እውቀቶች አካል መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ሥርዓቱ በዜጎች መካከል የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበት መሳሪያ ሆኖ እያገለገለ እንደሚገኝ አመልክተዋል።

"እነዚህ ትውልድ ተሻጋሪ የሆኑና በሀገር ግንባታ ውስጥ ተተኪ ሚና የሌላቸው ባህላዊ ሀብቶች ለዘመናት ዘርፉን የሚመጥን ትኩረት ሳያገኙ ቆይተዋል" ብለዋል።

ሚኒስቴሩ ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመቀጠቀም የሀገሪቱ ባህላዊ ሀብቶችን በማጥናት፣ በመጠበቅና በማልማት ለቀጣዩ ትውልድ እንዲተላለፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ሚኒስቴሩ በሀገሪቱ ሁለንተናዊ እድገት ውስጥ ባህል ቁልፍ ሚና እንዲጫወት ፖሊሲዎች፣ ስትራቴጂዎችና የህግ ማዕቀፎች በመዘርጋት ተግባራዊ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደሚገኝ ሚኒስትር ዴኤታዋ ተናግረዋል።

የህዝብ ሀብት የሆነውን ባህላዊ እርቅ ለመላው ዓለም ለማስተዋወቅና ለሀገር ዘላቂ ሠላም የሚኖረውን ፋይዳ ለማጉላት ሥርዓቱን ወደ ፊልም ኢንዱስትሪ ለማስገባት ስራ መጀመሩን ጠቁመዋል።

የሲዳማ ክልል ባህል፣ ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃጎ አገኘሁ በበኩላቸው በሀገሪቱ ተዝቆ ከማያልቅ ባህላዊ ስርዓቶች ውስጥ የባህላዊ የዳኝነትና የግጭት አፈታት ሥርዓት ዋንኛው መሆኑን ተናግረዋል።

የሲዳማ ህዝብ ''አፍኔ'' የተሰኘ የግጭት መፍቻ ሥርዓት እንዳለው የጠቆሙት የቢሮው ሃላፊ ስርአቱ አብሮነትን ከማጠናከርና ባህልና ወግ ጠብቆ በማቆየት የሲዳማ ህዝብን የሰላም ተምሳሌት እንዲሆን ማስቻሉን አመልክተዋል።

ከውይይት መድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የቱለማ አባገዳ ጎበና ሆላአሬሶ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት ባህላዊ ሥርዓቱ እርቅና ሠላም በማውረድ ህብረተሰቡን ለማቀራረብና በሀቅ ላይ የተመሰረተ ፍትህ በመስጠት የበኩሉን ሚና ሲጫወት ቆይቷል።

የዚህ ዓይነቱ የውይይት መድረክም የግጭት አፈታት ክህሎትን ለማሳደግና በሂደትም የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችሉ ገንቢ ሀሳቦች ለመቅሰም እንደሚረዳ ጠቁመዋል። 

ባህላዊ እምቅ ሀብቶችን ለይቶ በማልማት የውስጥ ችግሮችን በውስጣዊ አቅምና ክህሎት የመፍታት አቅም መገንባት እንደሚያስፈልግ የተናገሩት ደግሞ የጥንታዊት ጀግኖች አርበኞች ማህበር ፕሬዚዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን ናቸው።

ባለፉት 27 ዓመታት የሀገሪቱን ባህል ለመሸርሸር የተፈጸሙ ሴራዎችን ለማምከን ይህን መሰሉ የውይይት መድረክ እስከ ትምህርት ቤት ድረስ በየደረጃው ሊስፋፋ እንደሚገባ አመልክተዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም