በላልይበላ የገና በዓልን በድምቀት ለማክበር የሚያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታ ተጠናቋል

53

ባህርዳር፣ ታህሳስ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) በታሪካዊቷ የላልይበላ ከተማ የገና በዓልን ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘቱን ጠብቆ በድምቀት ለማክበር የሚያስችል የመሰረተ ልማት ዝርጋታ መጠናቀቁን የአማራ ክልል ቱሪዝም ቢሮ አስታወቀ።

የቢሮው ምክትል ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ መኮንን ዛሬ በሰጡት መግለጫ እንዳሉት፤ የላልይበላ ከተማ ለረጅም ጊዜ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ስር በመቆየቱ መጠነ ሰፊ የመሰረተ ልማት ውደመት ደርሶበታል።

በአሁኑ ወቅት የወደሙ የውሃ፣ የቴሌኮም፣ የመብራትና ሌሎች መሰረተ ልማቶች ተጠግነውና ተሟልተው ለአገልግሎት መብቃታቸውን ተናግረዋል።

የመሰረተ ልማቶቹ አገልግሎት መጀመር ሆቴሎችና ሌሎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ለበዓሉ የሚመጡ እንግዶችን በኢትዮጵያዊ የእንግዳ አቀባበል ባህል መሰረት ለማስተናገድ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክተዋል።

የኢንተርኔትና የስልክ አገልግሎቶች ክፍት በመደረጋቸውም የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች ከአለም አቀፉም ሆነ ከአገር ውስጥ ማህበረሰብ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት የተሳለጠ እንደሚያደርገውም ጠቅሰዋል።

የአገር ውስጥና የውጭ ጎብኝዎች የገና በዓልን ለማክበር ወደ ከተማዋ እየገቡ መሆናቸውን  ጠቁመው፤ የፌደራልና የክልል ተቋማት በከተማዋ የመሰረተ ልማት የማሟላት ስራቸውን በተሳካ ሁኔታ በማጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ በመወጣታቸው ምስጋና አቅርበዋል።

በቀጣይም ጥምቀትን በጎንደር፣ የግዮን በዓልን በሰከላና ረጅም ዘመን ያስቆጠረው የአገው ፈረሰኞች ማህበር በዓልን በእንጅባራ ከተማ በድምቀት ለማክበር ዝግጅት እየተደረገ በመሆኑ እንግዶች እንዲታደሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም