ፍርድ ቤቱ ሰው የማገት ወንጀል ፈጽመዋል ያላቸውን ሶስት ወንድማማቾች በእስራት ቀጣ

88

መተማ፤ ታህሳስ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) የምዕራብ ጎንደር ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሰው የማገት ወንጀል ፈጽመዋል ያላቸውን ሶስት ወንድማማቾች እያንዳንዳቸውን በ18 ዓመት ጽኑ እስራት ቀጣ።

የፍርድ ቤቱ የህዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ አበበ ማስሬ ለኢዜአ እንደገለጹት ወንድማማቾቹ በተከሰሱበት ወንጀል ጥፋተኝነታቸው በማስረጃ በመረጋገጡ የቅጣት ውሳኔ ተላልፎባቸዋል።

"ወንድማማቾቹ በመተማ ወረዳ ህዳር 30 ቀን 2014 ዓም በግምት ምሽት 4 ሰዓት ላይ የማሽላ ምርት ወቅተው አውድማ በመጠበቅ ላይ የነበሩ የ14 ዓመት ታዳጊ ህፃንና አንድ ሌላ ግለሰብ ላይ የእገታ ወንጀል በመፈጸማቸው ቅጣት ተላልፎባቸዋል" ብለዋል ።

ለጊዜው ካልተያዙ ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመሆን ወንጀሉን የፈፀሙት 1ኛ ተከሳሽ መልኬ መካሻው የጦር መሳሪያ በመያዝ፣ 2ኛ ነጋ መካሻውና 3ኛ ተከሳሽ ታከለ መካሻው የተባሉ ወንድማማቾች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

ግለሰቦቹ ተበዳዮችን እጃቸውን አስረው በጫካ በማቆየትና ለጊዜው 50 ሺህ ብር ከቤተሰቦቻቸው ተቀብለው ለሌላ አጋቾች አሳልፈው መስጠታቸው መረጋገጡን ገልፀዋል።

ከታዳጊ ህፃኑ ጋር የታገተው ግለሰብ ከ3 ቀን ቆይታ በኋላ ታህሳስ 3 ቀን 2014 ዓም በግምት ከሌሊቱ 8:00 ሾልኮ በማምለጥ እራሱን ማዳን እንደቻለ ተናግረዋል።

አጋቾቹ ታዳጊ ህፃኑን ደብቀው ከማሰቃየታቸው በላይ ከቤተሰቦቹ 160 ሺህ ብር ተቀብለው እንደለቀቁት ማስረጃ መረጋገጡን አብራርተዋል።

ወንድማማቾቹ ወንጀሉን ከፈፀሙ በኋላ ለጊዜው ከአካባቢው ቢሰወሩም ፖሊስ ባደረገባቸው ክትትል ታህሳስ 9 ቀን 2014 ዓ.ም በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸው ባለሙያው አስረድተዋል።

"አቃቢ ህግ በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማስደገፍ በወንድማማቾች ላይ የመሰረተውን ክስ የተመለከተው የዞኑ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የወንጀል መቅጫ 1995/590 ሐ ተላልፈው በመገኘታቸው ጥፋተኝነታቸውን አረጓግጧል" ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ ዛሬ ባስቻለው ችሎት ጥፋተኛ ባላቸው ሶስት ወንድማማቾች ላይ እያንዳንዳቸውን በ18 ዓመት ፅኑ እስራት እንዲቀጡ ውሳኔ ማሳለፉን ባለሙያው አስታውቀዋል።

እንደ ባለሙያው ገለጻ ፍርድ ቤቱ  በወንጀሉ ተሳትፈዋል የተባሉ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ተይዘው ለህግ እንዲቀርቡ ለፖሊስ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም