በአገር ቤት ቆይታችን ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ ኤምባሲዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥያቄ እናቀርባለን

65

ታህሳስ 26/2014/ኢዜአ/ በአገር ቤት ቆይታችን ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ ኤምባሲዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥያቄ እናቀርባለን ሲሉ የ"ዲፌንድ ኢትዮጵያ " አባላት ተናገሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ያደረጉትን ጥሪ ተከትሎ በተለያዩ የዓለም አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን፣ ትውልደ ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች ወደ አገር ቤት እየገቡ ነው።

ወደ አገር ቤት ከገቡ የዳያስፖራ ማህበረሰብ አባላት መካከል በ12 የአውሮፓ አገራት በመንቀሳቀስ የኢትዮጵያን እውነት ለማሳወቅ የሚሰራው "ዲፌንድ ኢትዮጵያ" አባላት ይገኙበታል።

የቡድኑ አባላት እንደሚሉት፤ በአገር ቤት ቆይታቸው መቀመጫቸውን አዲስ አበባ አድርገው ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ ኤምባሲዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥሪ ያቀርባሉ፡፡

በእንግሊዝ የ"ዲፌንድ ኢትዮጵያ" ተጠሪ አቶ ዘላለም ተሰማ፤ ቡድኑ የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ከማሳወቅ ባለፈ ምዕራባዊያን በአፍሪካ አገራት ላይ ያላቸውን የተሳሳተ አካሄድ እንዲያስተካክሉ እንደሚታገል ተናግረዋል፡፡

ቡድኑ በኢትዮጵያ የሚገኙ የአውሮፓ አገራት አምባሳደሮች ጋር ለመወያየት እየተንቀሳቀሰ መሆኑንና በዚህም ጥያቄያቸውን በአካል ለማቅረብ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

ውይይቱ የማይሳካ ከሆነ ደግሞ ኢትዮጵያን በተመለከተ የተሳሳተ መረጃ የሚያሰራጩ ኤምባሲዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ ጥያቄያቸውን በጽሁፍ እንደሚያቀርቡ አብራርተዋል፡፡

ለአሸባሪው ህወሃት ድጋፍ የሚሰጡ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡና አሸባሪ ቡድኑ ያደረሰውን ሰብዓዊና ቁሳዊ ውድመት እንዲያወግዙ እንደሚጠይቁም ጨምረው ገልጸዋል፡፡

አሸባሪ ቡድኑ ያወደማቸውን አካባቢዎች መልሶ ለማቋቋም የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉም እንዲሁ፡፡

ኢትዮጵያ እየተደረገባት ያለውን ጫና በማሸነፍ ዳግም የአፍሪካ ነጻነት ምሳሌ እንደምትሆን ያላቸውን እምነት የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የቡድኑ አባል አቶ ዘላለም ጌታሁን ናቸው።

በጀርመን አገር የሚኖሩት ወይዘሮ አስቴር ሮዝስታር በበኩላቸው አሸባሪው ህወሃት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ እንዳይሳተፍ ሲሰራ መቆየቱን አንስተዋል፡፡

አሁን ላይ ዳያስፖራው በአገሩ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳታፊ መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በተመሳሳይ በአሜሪካ ቺካጎ ነዋሪ የሆኑት አቶ የሱፍ ሃሰን፤ አገር በተቸገረችበት ጊዜ መድረስ በታሪክ ትልቅ ትርጉም የሚሰጠው ጉዳይ መሆኑን  ተናግረዋል፡፡

በመሆኑም ዳያስፖራው በሚችለው አቅም አገሩን መደገፍ እንደሚጠበቅበት ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢፌዴሪ ቱሪዝም ሚኒስትር ደኤታ ወይዘሮ ሰላማዊት ዳዊት በበኩላቸው ዳያስፖራው የገና በዓልን በኢትዮጵያ ለማክበር በስፋት ወደ አገር ቤት እየገባ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዳያስፖራው የኢትዮጵያን እውነት ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ መሆኑን  ገልጸው፤ ይህን ይበልጥ ለማጠናከር በቅንጅት እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም