ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለሰራዊቱና ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች 10 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ አደረገ

79

ታህሳስ 26 ቀን 2014 (ኢዜአ) ብርሃንና ሰላም ማተሚያ ድርጅት ለአገር መከላከያ ሰራዊትና አሸባሪው ህወሃት ፈጽሞት በነበረው ወረራ ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች 10 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ አደረገ፡፡

የድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽታሁን ዋለ ድጋፉ የድርጅቱን 100ኛ ዓመት በዓል ለማክበር ከተዘጋጀው በጀት ላይ በመቀነስ እንዲሁም ከሠራተኛውና ከቁጠባ ማህበር መዋጮ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ድርጅቱ በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ወቅት ጉዳት ለደረሰባቸው ዜጎች 5 ነጥብ 7 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ የምግብ ነክ ቁሳቁስ ባለፈው ሳምንት ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰው፤ በዛሬው እለትም ለሰራዊቱ 4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል።

ድጋፉን የተረከቡት የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ ለመከላከያ ሠራዊት ያደረገው ድጋፍ የሚያስመሰግነው መሆኑን ተናግረዋል።

በተለይ ድርጅቱ የ100ኛ ዓመት በዓሉን በማስመልከት የሚወጣውን ወጪ ለዚህ በጎ ተግባር እንዲውል ማድረጉ አርአያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

''ድርጅቱ ላደረገው ድጋፍ በመከላከያ ሠራዊታችንና በመላው የኢትዮጵያ ህዝብ ስም ምስጋና እናቀርባለን'' ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ፤ ይኸው ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተያያዘም የብረታ ብረትና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ከመከላከያ ኢንጂነሪንግ ኮሌጅ ተመራቂዎች ማህበር ጋር በመተባበር ለሰራዊቱ የሚውል ከ250 ሺህ ብር በላይ የሚያወጣ የአይነት ድጋፍ አድርጓል።

ድጋፉን የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሺሰማ ገብረሥላሴና  የብረታ ብረትና ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር አስፋው ረጋሳ አስረክበዋል፡፡

ተቋማቱ ከዚህ ቀደም ለሰራዊቱ የተለያዩ ድጋፎችን ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም