በዞኑ 484 ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ ተጀምሯል

93

ጊምቢ ታሕሳስ 26/2014(ኢዜአ) በምዕራብ ወለጋ ዞን 484 ተፋሰሶችን መሰረት ያደረገ የበጋ ወቅት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ሥራ መጀመሩን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በዞኑ ዛሬ የተጀመረው የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራ ለመጭዎቹ ሁለት ወራት የሚካሄድ መሆኑ ተነግሯል ፡፡

በጽህፈት ቤቱ  የተፈጥሮ ሃብት ቡድን መሪ አቶ ፍቅሩ ብርሃኑ ለኢዜአ እንደገለጹት የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራው በዞኑ በ20  ወረዳዎች 300 ሄክታር መሬት ባካለለ መልኩ ይካሄዳል ።

የተፈጥሮ ሀብት ልማትና ጥበቃ ስራው የማሳ ውስጥና የጋራ ላይ እርከን ጨምሮ የመሬት ርጥበትን ለመጠበቅና ለአካባቢ ጥበቃ የሚረዱ ሌሎች የአፈርና ውሃ ጥበቃ ሥራዎች  እንደሚከናወኑ ተናግረዋል።

በተጨማሪም 24ሺህ 785 ሄክታር  የተጎዳ መሬት ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ የማካለል ስራ እንደሚካሄድ ጠቅሰዋል ።

በዘመቻ በሚካደው የልማት ስራ ከ281ሺህ በላይ አርሶ አደሮች እንደሚሳተፉ ቡድን መሪው አመልክተዋል ።

በዞኑ የሆማ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ጉተማ ቀልቤሳ በሰጡት አስተያየት ባለፉት ዓመታት በመርሐ ግብሩ ተሳትፈው ባዩት ውጤት በመበረታታት ዘንድሮም መሳተፍ መጀመራቸውን ተናግረዋል።

ባለፉት አመታት በወል ይዞታዎች ላይ በተሰራ እርከንና ችግኝ ተከላ ገላጣማ ስፍራዎች ወደ አረንጓዴነት መቀየራቸውንና የደረቁ ኩሬዎችም በውሀ መሞላታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

ባለፉት አመታት በተካሄዱ የማሳ ውስጥ እርከን ስራዎች ለሰብል ምርት መጨመር አስተዋጾ ማድረጋቸውን የገለጹት ደግሞ የላሎ ጊምቢ ወረዳ ነዋሪ አርሶ አደር ሚዛኑ ቶሌራ ናቸው።

በማሳቸው ውስጥ ባከናወኑት የእርከን ሥራ ወደ አሲዳማነት ተቀይሮ የነበረው የእርሻ መሬታቸው ለምነቱ በመመለሱ የተሻለ ምርት ማግኘት መጀመራቸውን ተናግረዋል ።

ዘንድሮም ከግል ማሳቸው በተጨማሪ በወል ይዞታዎች በሚካሄዱ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራዎች እንደሚሳተፉ አርሶ አደር ሚዛኑ አስታውቀዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም