በኮንሶ ዞን በያልዳ ሸለቆ ከ2 እስከ 3 ሚሊየን አመት ያስቆጠረ ቅሪት አካል ተገኘ

159

ታህሳስ 26/2014/ኢዜአ/ በደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶ ዞን በያልዳ ሸለቆ ከ2 እስከ 3 ሚሊየን አመት ያስቆጠረ ቅሪት አካል ተገኘ።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሶሻል ሳይንስ ትምህርት ክፍል ባደረገው የጥናት ግኝት ከ2 እስከ 3 ሚሊየን አመት እድሜ ያስቆጠረ የእንስሳት ቅሪት አካል እና ሰዎች ሲገለገሉባቸው የነበሩ የድንጋይ መሳሪያዎች መገኘታቸው ተረጋግጧል።፡

የምርምር ቡድኑን የመሩት ዶክተር ዓለምሰገድ በልዳዶስ፤ የቅሪት አካሉ በደቡብ ኢትዮጵያ ኮንሶ ዞን በያልዳ ሸለቆ መገኘቱን ገልጸዋል።

በማብራሪያቸውም ከ2 እስከ 3 ሚሊየን አመት እድሜ ያለው የእንስሳት ቅሪት አካልና በጥንት ጊዜ ሰዎች ሲገለገሉባቸው የነበሩ የድንጋይ መሳሪያዎች ተገኝተዋል ብለዋል።

የቅሪት አካሉ ግኝት ከሚሊዮን አመታት በፊት ይኖሩ የነበሩ የእንሰሳት ዝርያዎችን ማወቅና መለየት የሚያስችል መሆኑንም ጠቅሰዋል።

አዲሱ ግኝት ከቅሪት አካል እና የድንጋይ መሳሪያ ክምችቱ እንዲሁም ክምችቱ ከተገኘበት ውስን መልክዓ ምድር አንጻር ሲታይ በኢትዮጵያ እስካሁን ከተገኙት በግንባር ቀደምትነት ሊመደብ የሚችል መሆኑ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና፤ አዲሱ ግኝት ለኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ እድገት ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡

የጥናት ውጤቱ ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ከፍተኛ ጥቅም የሚሰጥ መሆኑን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ተናግረዋል።

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የቅሪት አካሉን ግኝት ለቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለስልጣን አስረክቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም