የመንግስት ተቋማት የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማፋጣን የአገልግሎት አሰጣጥ አሰራራቸውን ውጤታማ ማድረግ አለባቸው

97
አዲስ አበባ ነሀሴ 21/2010 በኢትዮጵያ  የተጀመረውን ለውጥ ለማፋጣን የመንግስት ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ አሰራራቸውን በቴክኖሎጂ የተደገፈ፣  ቀልጣፋና ውጤታማ ማድረግ እንደሚጠበቅባቸው የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሃብት ልማት ሚኒስቴር አሳሰበ። ሚኒስቴሩ ከፌደራል ተቋማት ለተወጣጡ መካከለኛ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች በውጤታማ የአገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ በቢሾፍቱ ከተማ ለ10 ቀናት የሚቆይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ ነው። በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ከፍያለው ተፈራ እንደተናገሩት የመንግስት ተቋማት ለአገሪቱ ዕድገት መፋጠን የጎላ ድርሻ ያላቸው በመሆኑ አገልግሎት አሰጣጣቸውን ማዘመን አለባቸው። ይሁን እንጂ በአሁኑ ሰዓት ቴክኖሎጂው ከደረሰበት እድገት አንጻር በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ አብዛኞቹ  የመንግስት ተቋማት የቴክኖሎጂ አጠቃቀማቸው ውስን በመሆኑ በሚፈለገው መጠን አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ ሚኒስትር ዴኤታው ተናግረዋል። በመሆኑም የፌዴራል ተቋማት አገልግሎት አሰጣጣቸውን በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የታገዘ፣ ቀልጣፋና ጥራት ያለው በማድረግ የህብረተሰቡን የመልካም አስተዳደር ችግር ለመፍታትና የተጀመረውን ለውጥ ለማገዝ የበኩላቸውን ዝግጁነት ማረጋገጥ እንዳለባቸው አስገንዝበዋል። ተቋማቱ ዓለም አቀፍ ጥራቱን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት የተጣለባቸውን አገራዊ ተልዕኮ በብቃት መወጣት አለባቸውም ብለዋል። እንዲህ ዓይነቱ አገልግሎት የተጀመረውን አገራዊ ለውጥ ለማፋጣን የሚያግዝ መሆኑን የገለፁት አቶ ከፍያለው ተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ አሰራራቸውን ውጤታማ ለማድረግ በመስኩ የሚሰጡ ስልጠናዎች ዓይነተኛ ሚና እንደሚኖራቸውም አመልክተዋል። ለመንግስት ተቋማት መካከለኛ አመራሮችና ከፍተኛ ባለሙያዎች እየተሰጠ ያለው ስልጠና ተቋማት እርስ በእርሳቸው ልምድ እንዲቀስሙ የሚያግዛቸው ነው ተብሏል። ከዚህም ሌላ ስልጠናው አቅማቸውን በማጠናከርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ብቃታቸውን በማሳደግ  የአገልግሎት አሰጣጥ በየፊናቸው ያለውን የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት ቀልጣፋና ውጤታማ ለማድረግ የሚያግዝ ነው ተብሏል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም