ሀገርን በሁሉም መስክ ለማሻገር የድርሻችንን እንወጣለን

83

ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) የህዝቡን የመልካም አስተዳደርና የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ብሎም ሀገርን ለማሻገር የተጀመረውን ጉዞ ለማሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ አስተዳደር የመንግስት ሠራተኞች አስታወቁ።

ሠራተኞቹ በወቅታዊ ሀገራዊና አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ዛሬ ከከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች ጋር ተወያይተዋል።

በውይይቱ የተሳተፉት ሠራተኞች ለኢዜአ እንደገለጹት በአፋር እና በአማራ ክልል የተጎዱ ወገኖችን መልሶ ለማቋቋም አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ተዘጋጅተዋል።

እንደ ሠራተኞቹ ገለጻ የደጀንነት ስራቸውን ከማጠናከር ባለፈ የተጣለባቸውን ህዝባዊና መንግስታዊ ኃላፊነት ዳር ለማድረስ ቁርጠኛ ናቸው።

ከሠራተኞቹ መካከል አቶ ሰለሞን ደመላሽ በሰጡት አስተያየት "የህዝብን ጥያቄዎች መመለሰ የሀገርን ህልውና ለማቆየትና የተጀመረውን የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል ፋይዳው የጎላ ይሆናል" ብለዋል።

"እኔ የትኛውንም መስዋዕት ከፍዬ ለትውልዱ የተሻለች ሀገር ማስረከብ እፈልጋለሁ፤ ዘንድሮ በስራዬ ውጤታማ በመሆን ተገልጋዩን ለማርካት እተጋለሁ" ነው ያሉት።

አቶ ሙክታር አሊ በበኩላቸው "አሸባሪዎቹ ህወሓት እና ሸኔ የአካባቢውን ሰላም ለመናድ የሚያደርጉትን ትንኮሳና የወሬ አሉባልታ በተባበረ አንድነት ማክሸፋችንን እንቀጥላለን" ብለዋል።

ለዘላቂ ሰላም የአካባቢያቸውን ሰላም በአስተማማኝ መንገድ ከመጠበቅ ጀምሮ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል መዘጋጀታቸውን የገለጹት ደግሞ ወይዘሮ አበባ አለማለሁ እና አቶ ሁሴን መሐመድ ናቸው።

ውይይቱን የመሩት የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች በበኩላቸው፣ ለዘላቂ ሰላምና ልማት መረጋገጥ እንዲሁም ሀብትን ለታመለት ዓላማ በቁጠባ ለማዋል ሠራተኛው በቁርጠኝነት እንዲሰራ አሳስበዋል።

የመንግሥት ሠራተኛው በየደረጃው በተሰማራበት መስክ ሁሉ ውጤት እንዲመዘገብ መትጋት እንዳለበት አስገንዝበዋል።

ዛሬ በድሬዳዋ በተካሄዱ የተለያዩ ውይይቶች ከ2 ሺህ በላይ የአስተዳደሩ ሠራተኞች መሳተፋቸው ተገልጿል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም