በአማራ ክልል በአሸባሪው ህወሓት ወረራ ስር በነበሩ ዞኖች ተቋማትን ወደ አገልግሎት ለማስገባት እየተሰራ ነው

46

ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት በወረራ ይዟቸው በነበሩ ዞኖች አገልግሎት ሰጭ ተቋማትን በፍጥነት ወደ አገልግሎት ለማስገባት እየተሰራ መሆኑን ክልሉ ገልጿል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ የማህበራዊ ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ስዩም መኮንን ማምሻውን በሰጡት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ በአሸባሪው የህወሓት ቡድን ወረራና ውድመት የደረሰባቸውን አካባቢዎች መልሶ የመገንባት ሥራ እየተካሄደ ነው።

የሽብር ቡድኑ ከሰኔ ወር 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአማራ ክልል ወረራ በፈጸመባቸው ሰባት ዞኖችና አንድ ከተማ አስተዳደር ጭካኔ የተሞላበት ዘረፋና ውድመት አድርሷል ሲሉ አውስተዋል።

በክልሉ ለመስማት የሚከብዱ ሰብዓዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳቶችን በማድረስ በአማራ ክልል ህዝብ ላይ ከፍተኛ የጥፋት ተግባር መፈጸሙን አስረድተዋል።

የሽብር ቡድኑ በወረራ በቆየባቸው አካባቢዎች ተፈናቃዮችን ጨምሮ ከ11 ነጥብ 4 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ለችግር ማጋለጡን አመልክተዋል።

አሸባሪው ሃይል በጦርነቱ ተሸንፎ በወረራ የያዛቸውን አካባቢዎች ለቆ ከወጣ በኋላ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት የሚያስችል እንቅስቃሴ መጀመሩን አስተባባሪው ገልጸዋል።

በተለይም ለህዝብ ግልጋሎት የሚሰጡ ተቋማት ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ በተቀናጀ አግባብ እየተሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

በየአካባቢው መደበኛ የሰላም ማስከበርና የህግ የበላይነትን የማረጋገጥ ሥራም እንዲሁ።

ሌሎች የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ባሉበት አቅም ፈጥነው ወደ ሥራ እንዲገቡ ያልተቆጠበ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አህመድ ጥሪን በመቀበል ወደ ሀገራቸው የሚመጡ ዳያስፖራዎች በመልሶ ማልማትና ማቋቋም ሥራው የበኩላቸውን እንዲወጡ የማመቻቸት ስራ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ወገኖችን መልሶ ማቋቋም፣ የወደሙ ተቋማትን ወደ አገልግሎት የማስገባትና ሌሎች ሥራዎች በመንግስት አቅም ብቻ የሚቻል ባለመሆኑ መላው ህዝብ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያን እናልማ፣እንገንባ፣እንዘጋጅ

‼️

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ

‼️

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ

‼️

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ

‼️
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም