ለሰራዊቱ እስካሁን ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ እና ከ971 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነት ድጋፍ ከህዝቡ ተደርጓል

76

ታህሳስ 25 ቀን 2014 (ኢዜአ) ለአገር መከላከያ ሰራዊት እስካሁን ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ እና ከ971 ሚሊዮን ብር በላይ የአይነት ድጋፍ በህዝቡ መደረጉን የአገር መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ የኀብረተሰቡን ድጋፍ አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ ኢትዮጵያዊያን ከጫፍ ጫፍ አንድ በመሆን ለሰራዊቱ ያላቸውን ደጀንነት በተግባር አሳይተዋል ብለዋል።

የህልውና ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ እስካሁን ድረስ ለሰራዊቱ 971 ሚሊዮን 500 ሺህ ብር የሚገመት የአይነት ድጋፍ ከህዝቡ መደረጉን ተናግረዋል።

ይህም ኢትዮጵያዊያን ለመከላከያ ሰራዊት ያላቸውን አጋርነት በተግባር ያረጋገጠ ስለመሆኑ አንስተዋል፡፡

በተጨማሪም ለሰራዊቱ ገቢ ማሰባሰቢያ በተከፈተው የባንክ አካውንት ከ2 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል፡፡   

"ይሄን መግለጫ እስከምሰጥበት ጊዜ ድረስ 2 ቢሊዮን 41 ሚሊዮን 155 ሺህ 16 ብር በመከላከያ ሚኒስቴር ማዕከል በተከፈተው 1000421912134 አካውንት ቁጥር ገቢ ተደርጓል" ብለዋል።  

በ6800 አጭር የጽሁፍ መልዕክት የገቢ ማሰባሰቢያም ከ200 ሺህ በላይ ዜጎች ድጋፍ ማድረጋቸውን ጠቅሰዋል።

በዚህም ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን ነው የተናገሩት።    

የኢትዮጵያ ህዝብ ለሰራዊቱ በተግባር እያሳየ ያለውን ደጀንነት አጠናክሮ እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርበዋል።  

ኢትዮጵያን እናልማ፣ እንገንባ፣ እንዘጋጅ‼

ሀገርን በዘላቂነት እናልማ‼

የፈረሰውን አብልጠን እንገንባ‼

ለማንኛውም ፈተና እንዘጋጅ‼

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም